የሱቶን ግምት፡ አርሰናል ሊቨርፑልን 4 ለ 1 ሊያሸንፍ ይችላል?

ታትሟል

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የማንቸስተር ደርቢ ሲቲ በበላይነት ያጠናቅቃል ማለቱ ተሳክቶለታል። በዚህ ሳምንትም በአርሰናል እና በሊቨርፑል ጨዋታ ትልቅ ግምት አስቀምጧል።

“ላውሮ ቀድሞ ግምቱን ያስቀምጥ ነበረው የስፖርት ተንታኝ) ሊቨርፑል ይሸነፋል ብሎ አይገምትም። እኔ ግን ይሸነፋሉ ሳይሆን ይቀጠቀጣሉ ነው የምለው” ይላል ሱቶን።

የሊጉ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እሑድ እና ሰኞ ይከናወናሉ።

ሱቶን እንደተለመደው በዚህ ሳምንትም እንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት አስቀምጧል።

ቅዳሜ

በርንማውዝ ከ ሌስተር

በየሳምንቱ በርንማውዝ ይሸነፋል እያልኩ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች አልተሸነፉም። ጎልም አላስተናገዱም።

ከቆመ ኳስ ሌስተር ላይ ስጋት ቢፈጥሩም ቀበሮዎቹ ምን መስራት እንደሚችሉ ከፎረስተ ጋር አሳይተዋል።

ፉክክር ያለበት ጨዋታ ይሆናል። በዚህ ጨዋታም በርንማውዝ ግምቴን የሚያፈርስ ውጤት ያስመዘግባል?

ግምት፡ 1 – 2

ቼልሲ ከ ዎልቭስ

ዎልቭሶች አሰልጣኝ በሩኖ ላዥን በጊዜ ማሰናበቱ ትንሽ ጭካኔ የሞላው ነው። ጎል ማስቆጠር አለመቻላቸው የአሰልጣኙ ጥፋት ሳይሆን የአጥቂዎቹ መጎዳት ነው።

ዎልቭስ አሰልጣኝ ያልተሾመላቸው ሲሆን ይህንን ጨዋታም አያሸንፉም።

ቼልሲም ከግርሃም ፖተር ጋር ህይወት የጀመረበት ወቅት ነው። ፒዬር-ኤምሪክ ኦባመያንግ ጎል ማስቆጠር ጀምሯል። ስለዚህ በቀላሉ ሦስት ነጥብ ያሳካሉ።

ግምት፡ 2 – 0

ማንቸስተር ሲቲ ከ ሳውዝሃምፕተን

የሳውዝሃምፕተኑ አለቃ ራልፍ ሃሰንሃትል ይባረራሉ የሚል ወሬ አለ። ከሲቲ ጋር መጫወት ደግሞ ትልቅ ዕድል ነው።

ቡድኑ ባለፈው ዓመት በሁለቱም ጨዋታ አቻ ቢለያዩም ዘንድሮ ግን ኢትሃድ ላይ አያሳኩትም።

የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን የጎሎቹን መጠን የቅርጫት ኳስ ሊያስመስለው ይችላል። ካለው የጨዋታ መደራረብ ግን በቂ ጎሎች ላይ ሲደርስ ቡድኑ ይቀዘቅዛል።

በዚህ ምክንያት ብዙ ጎል አልገምትም። ሲቲ በፍጥነት አራት ጎሎችን አስቆጥሮ ጨዋታውን መቆጣጠር የሚጀመር ይመስለኛል።

ግምት፡ 4 – 0

ኒውካስል ከ ብሬንትፎርድ

ባለፈው ሳምንት ኒውካስል ፉልሃምን ሲያሸንፍ ወደ ፊት የሚሄዱበት መንገድ አስገራሚ ነበር።

ካለም ዊልሰን ከጉዳት ተመልሶ ምርጥ ብቃት ላይ ሲገኝ ሚጌዌል አልሚሮን ደግሞ ካለፈው ዓመት ተሻሽሏል።

ኒውካስል ጨዋታውን በመቆጣጠር እና ዕድሎችን በመፍጠር ያሸንፋል።

የብሬንትፎርዱ አጥቂ ኢቫን ቶኒ ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ ሲመለስ ማረጋገጥ የሚፈለገው ነጥብ ይኖራል።

ግምት፡ 2 – 1

ብራይትን ከ ቶተንሃም

ብራይትን ድንቅ አቋም ላይ ስለሚገኝ ይህን ጨዋታ ለመገመት ከባድ ነው።

ሊያንድሮ ትሮሳድ አንፊልድ ላይ አስደናቂ ሆኖ ሲያመሽ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ደ ዜብሪም ማጥቃት የሚወዱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ቶተንሃም ዘንድሮ ማጥቃት ላይ የተመሠረተ አጨዋወት የሚመርጥ አይመስልም። የብራይተን አጨዋወት ግን ይመቻቸዋል።

ግምት፡ 1 – 1

እሑድ

ክሪስታል ፓላስ ከ ሊድስ

ይህን ጨዋታ ባለፈው ዓመት ዘግቤዋለሁ። ጨዋታው ሳቢ ካለመሆኑም በላይ 0 ለ 0 ነበር የተጠናቀቀው።

ይህም ድንቅ ጨዋታ አይሆንም። ውጤቱን በጣም የሚፈልጉት ፓላሶች ያሸነፋሉ ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 – 0

ዌስት ሃም ከ ፉልሃም

ዌስተሃም ባለፈው ሳምንት አስፈላጊ ነጥቦችን ከዎልቭስ ላይ ሰብስቧል።

መዶሻዎቹ በጥሩ አቋም ላይ ስለመሆናቸው ይህ ጨዋታ የሚፈተሹበት ይሆናል።

የፉልሃም ነገር የሚወሰነው በተጎዳው አጥቂያቸው አሌክሳንደር ሚትሮቪች ጤንነት ላይ ነው።

ግምት፡ 2 – 1

አርሰናል ከ ሊቨርፑል

አርሰናል ባለፈው ሳምንት ከቶተንሃም ጋር ነበረው ጨዋታ ላይ ሳቢ ነበር። በዚህ ጨዋታም በተመሳሳይ ይደግመዋል።

መድፈኞቹ በጥሩ አጨዋወት እና ልበ ሙሉነት ላይ ሲገኙ ቀያዮቹ ግን ነገሮች ገና አልተሰካኩላቸውም።

የርገን ክሎፕ ቡድን በቻምፒዮንስ ሊጉ ከሬንጀርስ ጋር ጥሩ ቢሆንም የተከላካይ መስመሩ አልተፈተነም። ማርቲኔሊ፣ ሳካ እና ጂሰስ ግን ፋታ የሚሰጧቸው አይመስልም።

ሊቨርፑል ጎል ማስቆጠር ቢችልም አርሰናል ባለው የማጥቃት መስመር ጥንካሬ የበላይ ሆኖ ያጠናቅቃል።

ግምት፡ 4 – 1

ኤቨርተን ከማንቸስተር ዩናይትድ

ኤቨርተን ባለፈው ሳምንት ጥሩ ብቃት ላይ ሳይሆንም ሳውዝሃምፕተንን ማሸነፍ ችሏል።

ብዙ ጎል ስለማይቆጠርባቸው ዕድሎችን ባይፈጥሩም በጨዋተ መቆየት ይችላሉ።

ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት በሲቲ የደረሰበት ሽንፈት ሁሉንም የሚያጋጥም ነው። ቡድኑ በኤሪክ ቴን ሃግ ስር የተወሰነ መሻሻል አሳይቷል።

ከአራት ድሎቻቸው በኋላ ይሰናከላሉ ብዬ አልጠብቅም። ሲቲን በመሰለ ቡድን በመሸነፋቸውም ችግር ውስጥ ናቸው አልልም።

ኤቨርተን በሜዳው የሚያጠቃ ቢመስለኝም ሁለቱም ቡድኖች ነጥብ ይጋራሉ።

ግምት፡ 1 – 1

ሰኞ

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ አስቶን ቪላ

የፎረስቱ አለቃ ስቲቭ ኩፐር በኃላፊነታቸው ቢቀጥሉም ነገሮች ጥሩ እየሄዱላቸው አይደለም።

በሌላ በኩል በአስር ተጫዋች ለ45 ደቂቃ ያህል የተጫወተውን ሊድስን ማሸነፍ ባለመቻሉ አስቶን ቪላ የሚገኝበትን ለማወቅ ያዳግታል።

ቡድኑ በሚጠበቀው ደረጃ አለመሻሻሉን የሚገልጹ ደጋፊዎች አሉ። ፊሊፔ ኮቲንሆም ዘንድሮ ጥሩ አቋም ላይ አይገኝም።

የፎረስት በራስ መተማመን ዝቀትኛ በመሆኑ ቪላ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

 ግምት፡ 0 – 1