አሜሪካ በዲሞክራቲክ ኮንጎ መጠለያ ጣቢያ ለደረሰ ጥቃት ሩዋንዳን ተጠያቂ አደረገች

መጠለያ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, መጠለያ ጣቢያው ጥቃትን በሸሹ ዜጎች የተሞላ ነው
ታትሟል

አሜሪካ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መጠለያ ጣቢያ ለደረሰ ጥቃት ሩዋንዳን ተጠያቂ አደረገች።

አሜሪካ ከሩዋንዳ ሌላ በዚህች አገር ይደገፋል የሚባለውን ''ኤም23'' የተባለውን ታጣቂ ቡድንንም ተጠያቂ አድርጋለች።

ከጎማ ከተማ በስተምሥራቅ በሚገኘው በዚህ መጠለያ ጣቢያ ጥቃት የደረሰው ባለፈው ዐርብ ነበር።

በጥቃቱ 9 ሰዎች ተገድለዋል። ከሟቾቹ መካከል ሰባት ሕጻናት ይገኙበታል።

የኮጎንጎ መከላከያ እና የኤም23 ታጣቂዎች ከጥቃቱ በኋላ እርስ በእርስ ተወነጃጅለዋል።

ጎረቤት ሩዋንዳ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሱትን ኤም23 አማጺያንን ትደግፋለች በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ይደርስባታል። ሩዋንዳ ግን ይህን ታስተባብላለች።

አሜሪካ እንደምትለው የዐርብ ዕለቱ ጥቃት የተሰነዘረው የሩዋንዳ መከላከያ እና የኤም23 አማጺዎች ከሚቆጣጠሯቸው ቀጠናዎች አቅጣጫ ነው።

አሜሪካ የሩዋንዳ መከላከያ ከአማጺው ጋር በመሆን በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እያደረጉ ያለውን መስፋፋት አሳስቦኛል ብላለች።

ሁለቱም አካላት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕጎችን እንዲያከብሩ ተማጽናለች።

አሜሪካ ባወጣችው መግለጫ፣ “ሁሉም አገሮች የሌላው አገር ሉአለዊነትና የግዛት አንድነትን ማክበር አለባቸው፣ ሰብአዊ መብትን የሚጥሱት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል” ብላለች።

ዐርብ ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ አስክሬኖች መሬት ላይ እዚያና እዚህ ወድቀው የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ሲዘዋወሩ ነበር።

በርካታ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎች ወደዚህ መጠለያ ጣቢያ ገብተው የሚኖሩት በየቀዬዎቻቸው የሚደረግን ዉጊያን በመሸሽ ነው።

የኮንጎ መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሌ/ኮ ንጂኬ ካይኮ፣ ጥቃቱ የተሰነዘረው ከዚህ ቀደም የኮንጎ መከላከያ በሩዋንዳ ጦር ሰፈር ላይ ለሰነዘረው ጥቃት በቀል እንዲሆን ነው ብለዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ለበርካታ ሳምንታት ውጭ ጉብኝት ላይ የነበሩት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ተብሏል።

''ኤሜ23'' ታጣቂ ቡድንና የኮንጎ መከላከያ ኃይል በምሥራቁ ክፍል ተጨማሪ ቦታን ለመያዝ በሚያደርጉት ጥረት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። በዚህም እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ።

የመጨረሻው ወሳኝ ጥቃት በኮንጎ መከላከያ የተሰነዘረው አማጺያኑ ሩባያ ከተማን ተቆጣጠርን ካሉ በኋላ ነበር።

ይህቺ ከተማ ሞባይልና የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎችን ለመሥራት የሚውለው እጅግ ተፈላጊ ማዕድን በስፋት የሚገኝባት መሆኗ ጠቃሚ ያደርጋታል።

''ኤም23'' አማጺ የተመሠረተው ከሌላ አማጺ ቡድን ተገንጥሎ ሲሆን በፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ የቱትሲ ተወላጆችን በምሥራቃዊ ኮንጎ ከሁቱዎች ጥቃት ለመጠበቅ ነበር።

በኪጋሊ የሚገኘው መንግሥትም በዋናነት በቱትሲዎች የሚመራና ይህንን አማጺ ቡድን የሚደግፍ ነው ይላል የተባበሩት መንግሥታት። ሩዋንዳ ግን ይህን ታስተባብላለች።

ይህ በእንዲህ እያለ በጎማ የተሰየመው ወታደራዊ ፍርድ ቤት ከአማጺያኑ በሚደረግ ፍልሚያ ''ክህደት ፈጽመዋል''፣ ''የመዋጋት ቁርጠኝነትና ወኔ ጎድሏቸዋል'' ያላቸውን ስምንት ወታደሮች በሞት እንዲቀጡ ወስኗል።