በደቡብ አፍሪካ ወደብ ላይ 19 ሺህ ከብቶች በፈጠሩት ጠረን ምክንያት ወደ ኢራቅ ተመለሱ

ታትሟል

በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ከተማ ከብቶችን የጫነች መርክብ ባስከተለችው የከፋ መጥፎ ጠረን ምክንያት ኬፕ ታውንን ለቃ ወደ ኢራቅ እንድትጓዝ መደረጉን የእንስሳትን ደህንነት የሚከታተል ተቋም ገልጿል።

አል ኩዌት የተሰኘችው መርከብ ባለፈው ዕሁድ ለጫነቻቸው 19 ሺህ ከብቶች መኖን ለማቅረብ ከብራዚል ወደ ደቡብ አፍሪካዋ የወደብ ከተማ ኬፕታውን ገብታለች።

ሆኖም ከትንሽ ቆይታ በኋላ ከመርከቧ የሚወጣው አጸያፊ ሽታ “እያቅለሸለሸን” ነው ሲሉ ነዋሪዎች ምሬታቸውን ማቅረብ ጀምሩ።

የእንስሳትን ደህንነት የሚከታተለው ተቋም መርከቡ ላይ ያሉትን ከብቶች ሁኔታ የገመገመ ሲሆን መርከቡ በከፍተኛ የከብቶች እዳሪ እና ሽንት እንደተሞላ ገልጿል። ሁኔታውንም “አጸያፊ” ሲል ገልጾታል።

በእንስሳት ላይ የሚፈጸሙ ጭካኔ የተሞላባቸው ተግባሮችን የሚከታተለው ተቋሙ ትላንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ከብቶቹ ለሁለት ሳምንታት ከሌሎች በርካታ እንስሳቶች ጋር እንደቆዩ ገልጾ እዳሪያቸው የሚጸዳበት ሁኔታ እንኳን አልነበረም ብሏል።

ጨምሮም ከባለፈው ዕሁድ እስከ ትላንት ማክሰኞ ግምገማውን በሚያካሂድበት ጊዜ “የተጎዱ እና የታመሙ” ከብቶች እንዳገኘም ገልጿል። ስምንት ከብቶች እንደተጎዱ እና የሞቱም እንዳሉ አሳውቋል።

“ይህ ክስተት እንስሳትን በባህር አማካኝነት ለውጪ ንግድ ማቅረብ ጊዜውን የማይመጥን እና ህይወት ባለቸው ፍጡራን ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ተግባር እንደሆነ የማንቂያ ደወል ሆኗል” ሲለም ተቋሙ ገልጿል።

ተቋሙ ጨምሮ በባህር እና መርከብ አማካኝንት የሚደረግ የቁም ከብት የውጪ ንግድ “ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ” ሊቀር ይገባል ብሏል።

በኬፕታውን የምትኖር አንዲት ነዋሪ ከአል ኪዊት ሲወጣ የነበረውን መጥፎ ጠረን በተመለከተ አስተያየቷን ስትሰጥ “በህይወቴ ሙሉ እንዲህ ያለ ሽታ ገጥሞኝ አያወቅም” ብላለች።

ጨምራም “ሽታው እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በጉሮሮዬ ላይ የቀረ የጥፎ ጣዕም ስሜት ይሰማኛል” ስትል ገልጻለች።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ፣ ከመርከቧ ሲመጣ በነበረው መጥፎ ጠረንም ምክያት ለመተንፈስ እጅግ ተቸግሬ ነበር ብሏል።