ለ24 ሰዓታት የቆየው ትርምስ፡ የቫግነር አለቃ መፈንቅለ-ፑቲን አስበው ነበር?

የፎቶው ባለመብት, CONCORD PRESS SERVICE
ሰኔ 17/2015 የምሕረት የለሹ ቫግነር ቅጥረኛ ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በፑቲን አስተዳደር ላይ አምጸው ወደ ሞስኮው 'ፍትሕን ፍለጋ' እየተጓዝኩ ነው ሲሉ ተነሱ።
የሩሲያው ፕሬዝደንት የቀድሞው ወዳጃቸውን ሃገር በመካድ ከሰሱት። “ከጀርባ ተወግተናል” ሲሉ ወቀሱ።
“በ24 ሰዓታት ለሞስኮ 200 ኪሎ ሜትር እስኪቀረን ተጉዘናል። ይህን ስናደርግ አንዲት ጠብታ ደም አላፈሰስንም” ሲሉ አወጁ።
ነገር ግን ቅዳሜ አመሻሹን ፕሪጎዢን ወታደሮቹ ሁሉን ነገር ትተው ወደ ካምፓቸው እንደሚለሱ ትዕዛዝ ሰጡ።
የቫግነር አለቃ መፈንቅለ-መንግሥት አስበው ነበር?
ፕሪጎዢን ይህ “ለፍትሕ የሚደረግ እርምጃ” ነው እንጂ መፈንቅለ መንግሥት አይደለም ይላሉ። ያም ሆነ ይህ በሩሲያ ተቀስቅሶ የነበረው ትርምስ በ24 ሰዓታት ተቋጭቷል።
ይህ ቅጠረኛ ቡድን ለወራት በዩክሬን የሩሲያ ወታደራዊ እርምጃን ሲያስተባብር፤ ሺዎችን በተለይ ከእሥር ቤት ለውትድርና ሲመለምል ቆይቷል።
የዚህ ቡድን መሪ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት ተከትሎ ከወታደራዊ መሪዎች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥም ገብተው ነበር።
ሰውየው ማንም ሳይስበው ወታደራዊ አስተዳደሩን በቁጥጥሬ ሥር አደርጋለሁ ሲሉ ዛቱ።
የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮች በተሽከርካሪ ከዩክሬን ወደ ግዙፏ የሩሲያ ሮስቶቭ-ኦን-ዶን ከተማ መንቀሳቀስ ጀመሩ።
ዓላማቸው ደግሞ ወደ ሞስኮው መገስገስ ነበር።
ብዙዎች ይህን ሲያዩ አንዳች ታሪክ ቀያሪ ነገር ሊፈጠር ይችላል የሚል ጥርጣሬ በውስጣቸው አሳደሩ። በለተይ ደግሞ በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ አዲስ ዜና ይሰማ ይሆናል አሉ።
የቫግነር ወታደራዊ ኃይል ወደ ሰሜን አቅጣጫ እየተጓዘ ሳለ የቤላሩሱ መሪ አሌዛሳንደር ሉካሼንኮ መሃል ገብተው ጉዳዩን አረጋጉት።
መፈንቅለ-መንግሥት ሊሆን ይችላል ተብሎ የተጠረጠረው አንቅስቃሴ በአንድ ቀን ይቀጫል ብሎ ማንም አልጠበቀም።
ነገር ግን እንደክሬምሊን ከሆነ ፕሪጎዢን በዩክሬን ጦርነትና በሩሲያ ያላቸው ቦታ ያበቃለት ይመስላል።
ሰውየው ወደ ቤላሩስ እንዲያቀኑ እና በእርሳቸውም ሆነ በወታደሮቻቸው ላይ ምንም ዓይነት ክስ እንደማይቀርብ ክሬምሊን አሳታውቋል። ወታደሮቹ ውል ይዘው የሩሲያ ጦር መቀላቀል ይችላሉ ተባለ።
ቫግነር እና የሩሲያ ወታደራዊ አለቃዎች?
ፕሪጎዢን ለወራት የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ እና የጦር ኃይሉን መሪ ቫለሪ ግራሲሞቭን ሲዘልፏቸው ቆይተዋል።
ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ለወታደሮቼ በቂ መለዮና የጦር መሣሪያ አልቀረበም የሚል ነው።
ፕሬዝደንት ፑቲን ዩክሬን ውስጥ እየተዋጉ ያሉ ሁሉም ቅጥረኛ ወታደሮች ፊርማ አኑረው በመከላከይ ሚኒስቴር ትዕዛዝ እንዲቀንሳቀሱ ሲሉ ፕሪጎዢን አሻፈረኝ አሉ።
ሰኔ 16/2015 ወጥተው ይህ ጦርነት ጥቂት ሙሰኞች ፕሬዝደንቱንና ሕዝቡን አጭበርብረው ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ ያደረጉት ነው ሲሉ ለመላ ሩሲያዊያን ድምጻቸውን አሰሙ።
ፕሪጎዢን ከዚህ አልፎ የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል ዩክሬን በሚገኙ የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ላይ እርምጃ ወስደዋል ሲሉ ወቁ።
የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል ወቀሳውን ችላ ብሎ ቫግነር የለጠፈው ተንቀሳቃሸው ምስል ምንም ማስረጃ ሊሆን እንደማይችል ገለጠ።
አርብ ማታ ፕሪጎዢን “ግስጋሴ ለፍትሕ” ሲሉ የሰየሙትን እንቅስቃሴ አወጁ።
“እኛ 25 ሺህ ነን። እናም ሃገራችን ለምን እንዲህ ያለው ውጥንቅጥ ውስጥ እንደገባች ለማጣራት እየገሰገስን ነው” የሚል ጥሪ አሰሙ። “የቻለ ይቀላቀለን” ሲሉ አከሉ።
ዩክሬን የሚገኙት የሩሲያ ጦር ኃይል ምክትል ጄኔራል ሰርጌ ሱሮቪኪን ሰውየው ረጋ ብሎ እንዲያስቡና ለፕሬዝደንት ፑቲን እንዲገዙ አሳሰቡ።
ነገር ግን ወደ ሮስቶች-ኦን-ዶን ያቀኑት ፕሪጎዢን በከተማዋ የሚገኘውን የዩክሬን ጦርነት የሚስተባበርበት ወታደራዊ መሥሪያ ቤት በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ገለጡ።
ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የሚለጠፉ ምስሎች እንሚያሳዩት የቫግነር ወታሮች በከተማዋ ያለማንም ከልካይ ይንቀሳቀሳሉ።
ቅዳሜ ማለዳ “አሁን ወደ ወታደራዊ ዋና መሥሪያ ቤት ገብተናል” ሲሉ አወጁ።
የሩሲያ ደኅንነን ቢሮ [ኤፍኤስቢ] የወንጀል መዝገብ ከፈተ። ሞስኮው በንቃት እንድትጠብቅ ተነገራት።
የፑቲን መልዕክት
ቅዳሜ ጥዋት እንደሁልጊዜው ድንጋጤ የማይነበብባቸው ፑቲን በቴሌቪዥን መስኮት ወጥተው ለሕዝባቸው ንግግር አሰሙ።
“እየገጠመን ያለው ከፍተኛ ክህደት ነው” አሉ። የቀድሞው አጋራቸውን ስም ሳይጠሩ ወታደራዊ ክህደት የሚፈፅሙ ዋጋ እንደሚከፍሉ ዛቱ።
ፕሪጎዢን መልስ ለመስጠት አልዘገዩም። እየፈፅምኩ ያለሁት ፈፅሞ ክህደት አይደለም ብለው ፕሬዝደንቱ “እጅግ ተሳስተዋል” የሚል መልዕክት አስተላለፉ።
ፕሪጎዢን እስከዛሬ የፑቲንን ስም አንስተው ነቅፏቸው አያውቁም። ቅዳሜ ዕለት ግን ይህን አደረጉት።
ሽሙጣዊ በሆነ መንገድ “ደስተኛው አያታችን” የሚል ቃል አወጡ። ለነገሩ ባለፈው ወርም እንዲሁ ሩሲያ በዚህ “ደደብ በሆነ አያት እየተመራች” እንዴት ታሸንፋለች ሱሉ ተዛልፈው ነበር።
የቫግነር ወታደሮች በወታደራዊ መኪና ተጭነው በቮሮኔዥ በኩል ወደ ሰሜናዊቷ ሊፔትስክ ከተማ ሲያመሩ ታዩ።
ቮሮኔዥ ከተማ ውስጥ አንድ የነዳጅ ቦቴ በእሣት ሲጋይ ቢታይም ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
የፑቲን አስተዳደር ፈተና?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሪጎዢን ደጋግመው እንደሚሉት የእርሳቸው ችግር ከዩክሬን ጦርነት ሳይሆን ጦርነቱን ከሚመሩት ጋር ነው።
ምንም እንኳ ያቀረቡት ጥያቄ እስካልተመለሰ ወደ ሞስኮው መግፋታቸውን እንደማይተዉ ቢያስታውቁም የፕሬዝዳንቱን አስተዳደር መገዳደር ዓላማቸው እንዳልነበር ይናገራሉ።
ለሰዓታት ፑቲን ሁኔታዎች ከእጃቸው ያመለጠ መሪ መስለው ነበር።
ነገር ግን ቅዳሜ ማታ የፑቲን አጋር የሆኑት የቤላሩሱ መሪ አሌክዛንደር ሉካሼንኮ መላ ይዘው መጡ።
ፕሪጎዢን ወደ ቤላሩስ አቀኑ። ምንም ዓይነት ክስ አይቀርብባቸውም ተባለ።
በስተመጨረሻም ሮስቶቭን በተሽከርካሪ ለቀው ሲወጡ ታዩ።
የቫግነር ወታደሮች እንዲሁ ምሕረት ይደርግላቸዋል። የፈቀዱ ደግሞ ለመከላከይ ሚኒስቴር ፊርማ አኑረው ይቀጥላሉ።
ፕሬዝደንት ፑቲን ከውጭ ሲታዩ 24 ሰዓታት በፈጀው የፕሪጎዢን አመፅ የደከሙ ይመስላሉ።
ከዚህ ውጥንቅጥ ለመውጣት የቤላሩሱ መሪን እርዳታ መጠየቃቸውም ግራ አጋቢ ነው። ቤላሩስ በተቃውሞ ስትናጥ የሉካሽንኮን ሕይወት ያራዘመችው ሩሲያ ናት።
አሁን ፕሪጎዢን የሉም። 25 ሺህ ገደማ ወታደሮችን ጥለው ከሩሲያ ወጥተዋል። ነገር ግን በሩሲያ ይሆናል ተብሎ የማይጠበቀው ሆኗል።












