ባለፉት አስር ዓመታት ከ1 ሺህ 700 በላይ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ተገድለዋል - ሪፖርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት አስር ዓመታት በእያንዳንዱ ሁለት ቀናት አንድ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እንደሚገደል አንድ አዲስ ጥናት አመለከተ።
ግሎባል ዊትነስ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዳለው የማዕድን ቁፋሮ፣ የነዳጅ ዘይት ማውጣትን አሊያም የመሬት ቅርምትን ለመከላከል ሲሞክሩ ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ባለፉት አስር ዓመታትም ብራዚል እና ኮሎምቢያ ከፍተኛ የሆነው የሞት ቁጥር ተመዝግቦባቸዋል።
አጥኝዎች ግን ቁጥሩ በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ጥቃት አያሳይም ብለዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የእንግሊዝ ጋዜጠኛ የሆነው ዶም ፊሊፕ እና የአካባቢው ባለሙያ ብሩኖ ፔሬራ መገደል ዓለም አቀፍን ትኩረት ስቦ ነበር። ወንጀሉ በብራዚል አማዞን አካባቢ ያለውን ሕገ ወጥ ድርጊት ያጋለጠ ነው ተብሏል።
ግሎባል ዊትነስ አዲስ ባወጣው ሪፖርት፣ ላቲን አሜሪካ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ዘመቻዎች በሚያካሂዱ እና ስለ አካባቢ በሚሟገቱ ሰዎች ላይ በተፈፀመ ግድያ በግንባር ቀደምትነት ተቀምጣለች።
68 በመቶ የሚሆነው ግድያ የተፈፀመው በአህጉሩ ውስጥ ሲሆን በብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ሜክሲኮ እና ሆንዱራስ ከፍተኛ ቁጥር መመዝገቡንም ጥናቱ አመልክቷል።
አብዛኞቹ የተገደሉት ሰዎች በማዕድን ቁፋሮ፣ በነዳጅ ዘይት ማውጣት አሊያም በሃይድሮ ፓወር አበልጻጊዎች ሳቢያ የመሬታቸውን መቀራመት ለመከላከል ሲታገሉ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው ብሏል።
ዓለም የዩክሬንን ጦርነትን ተከትሎ የተፈጥሮ ጋዝ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ አጥኝዎቹ ያምናሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ 2021 በአራት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 200 ሰዎች ተገድለዋል።
የግሎባል ዊትነስ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ሽሩቲ ሱረሽ “ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጥሮ ሃብት ጋር በተያያዘ ክፍተኛ ጭንቀት አለ። ይህም በተለይ በብራዚል አማዞን ላለው ግጭት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል” ብለዋል።
ሽሩቲ አክለውም በብራዚል የተፈፀመው 85 በመቶ ግድያ የተከሰተው በቀጠናው ነው ብለዋል።
“የዚህም ምክንያቱ ፍትሃዊ ያልሆነ የመሬት ክፍፍል ጉዳይ ነው። ሰዎች መሬታቸው እንዳይወሰድባቸው ይከላከላሉ።የተፈጥሮ ሃብትን ለመመዝበር ተጨማሪ መሬት ለማግኘት ትግሉን ጨምሮታል። በዚህም አብዛኞቹ ተጎጂዎች ድምጻቸው የታፈነው የአገሬው ሰዎች ናቸው” ሲሉ ሽሩቲ አክለዋል።
በ2021 የተገኙ ቁልፍ ግኝቶች
- በዓለም አቀፍ ደረጃ በየሳምንቱ በአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሳተፉ ወደ አራት የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።
- በብራዚል እና ሕንድ የሚፈፀመው ጥቃት እየጨመረ ሲሆን በኮሎምቢያ እና ፊሊፒንስ ደግሞ ቅናሽ ታይቷል።
- በአፍሪካ የተመዘገቡ አስር ግድያዎች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ የተከሰቱት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ነው። ከእነዚህ ሞቶች ውስጥ ስምንቱ በቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ የተፈፀሙ ሲሆን አብዛኞቹ የፓርክ ጠባቂዎች ናቸው።
- ግሎባል ዊትነስ፣ እንደ አውሮፓውያኑ 2021 በሕንድ የተፈፀመውን ሦስት ግድያ እና በሜክሲኮ የተፈፀመውን አራት ግድያዎችን ጨምሮ 12 የጅምላ ግድያዎች መዝግቧል።
- በኒካራጓ የወንጀለኛ ቡድኖች፣ በሚስኪቱ እና ማያንኛ ሕዝቦችን በመቃወም 15 የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን ገድለዋል።
ግሎባል ዊትነስ እንደሚለው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሁኔታ ለአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች አስከፊ ሆኗል።
ተሟጋቾችም፣ እየተባባሰ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ እና ሥ ምህዳር ቀውስ እንዲሁም አምባገነን በሆኑ መንግሥታት ሳቢያ ከ2018 ጀምሮ ያሉ ግድያዎች በተከታታይ መጨመሩን ተናግረዋል።
ከወንጀል እና ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር የተያያዙ ቡድኖችን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶች ለአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ግድያም እንደ ምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
ምንም እንኳን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግድያዎች ቁጥር መጨመር ቢኖርም ተሟጋቾች፣ ድርጊቱን በሚፈፅሙት ላይ እርምጃ እየተወሰደ በመሆኑ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።
ጨምረውም በአውሮፓ ኅብረት ኩባንያዎች አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ያሉና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፅሙ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሕግ ለማውጣት የተያዘውን እቅድም ጠቁመዋል።
ሽሩቲ “ እነዚህ ለአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች እውነተኛ እና አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ ውሳኔዎች ናቸው። የተስፋ ምልክቶች አሉ። ተስፋ ማድረግ አለብን፤ ቢሆንም ግን ወደፊት አስቸጋሪ እና ፈታኝ መንገድ ይጠብቀናል ” ብለዋል።












