የቻይና ምጣኔ ሃብት የተቀመጠለትን ግብ ስቶ አሽቆለቆለ

የፎቶው ባለመብት, VCG via Getty Images
የቻይና የምጣኔ ሃብት እድገት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ በደካማ የአገር ውስጥ ፍላጎት እና በኢራን ጦርነት ምክንያት ቀነሰ።
ይፋዊ የሆኑ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አሃዞች እንደሚያሳዩት፤ የዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት የሆነችው ቻይና መንግሥት ከያዘው የእድገት ግብ በመቀነስ ምጣኔ ሃብቷ በ4.3 በመቶ አድጓል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት በ5 በመቶ እድገት አስመዝግቧል።
ይህ የተባለው ባለፈው ሰኔ ወር የቻይና የወጪ ንግድ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ27 በመቶ ማመደጉን የመንግሥት መረጃ ካሳየ በኋላ ነው።
ባለፈው መጋቢት ቻይና የእድገቷን ዒላማ ከ4.5 እስከ 5 በመቶ ያደረገች ሲሆን፤ ይህም እ.አ.አ ከ1991 ወዲህ ዝቅተኛው የምጣኔ ሃብት ግብ ነው።
እርምጃውን አንዳንድ ተንታኞች የአገሪቱ መሪዎች ምጣኔ ሃብቱን ለማስተዳደር የተሻለ አወላዋይ እድል የሚሰጥ ነው ብለውታል።
የኢራን ጦርነት የካቲት 21/2018 ዓ. ም. ከተጀመረ ወዲህ ሙሉ የሩብ ዓመት የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት መረጃን የሚያሳይ እና አገሪቱ ከኮቪድ-19 ገደቦች በ2022 ከወጣች በኋላ ዝቅተኛው ነው።
የቻይና የስታስቲክ ብሔራዊ ቢሮ አሃዞችን ይፋ ሲያደርግ "በርካታ ውጫዊ አለመረጋጋቶች እና እርግጠኝነትን የቀነሱ ምክንያቶች አሉ" ብሏል።
በአገር ውስጥ ምጣኔ ሃብቱ በጠንካራ አቅርቦት እና በደካማ ፍላጎት መካከል የተዛባ ሚዛን እንዳለም አመልክቷል።
ከዚህ ውጭ ረቡዕ እለት ይፋ የሆነ መረጃ የቤጂንግ የንብረት ገበያው ማሽቆልቆልን እና የሸማቾች ደካማ ወጪን ጨምሮ በአገር ውስጥ የገጠማትን ምጣኔ ሃብታዊ ችግር የሚጠቁም ነው።
ምንም እንኳ የአዳዲስ ቤቶች ዋጋ በሰኔ ወር በ0.1 በመቶ የወረደ ቢሆንም በግንቦት ወር ከነበረው አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር እምብዛም አልቀነሰም።
የችርቻሮ ሽያጭ በሰኔ ወር በአንድ በመቶ ያደገ ሲሆን፤ ይህም በግንቦት ወር በ0.6 በመቶ ካሳየው ቅናሽ የተሻለ አፈፃፀም ነው።
ማክሰኞ እለት ይፋ የሆነው የሸማቾች መረጃ ለዳታ ማዕከላት ግንባታ የሚውሉ ሰሚኮንዳክተሮች ላይ በታየው ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት ምክንያት የቻይና የቴክኖሎጂ ምርቶች የወጪ ንግድ ጨምሯል።
ለቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያለው ከፍተኛ ፍላጎትም የቻይናን የወጪ ንግድ እንዲያድግ አድርጓል።
ወርሃዊ የተሽከርካሪዎች ሽያጭ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሚሊዮንን ተሻግሯል።















