የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ የሦስት ታጋቾችን አስክሬን ማግኘታቸው ተገለጸ

ታትሟል

የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ የሦስት ታጋቾችን አስክሬን ማግኘታቸውን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር አስታወቀ።

አስክሬኖቹ የሻኒ ሎውክ፣ አሚት ቡስኪላ እና ኢትዝሀክ ግሌርንተር መሆናቸው ተገልጿል።

ሐማስ ጥቃት የፈጸመበት ቀን ተገድለው አስክሬናቸው ወደ ጋዛ እንደተወሰደ የመከላከያ ሚኒስትር መግለጫ ይጠቁማል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን አስክሬኖቹ የተገኙት በሐማስ መተላለፊያ ዋሻ ውስጥ ነው ሲሉ ዘግበዋል።

ሐማስ ጥቃት በፈጸመበት ቀን 1,200 ሰዎች ተገድለዋል። 252 ሰዎች ወደ ጋዛ ታግተው ተወስደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዜናው “ልብ ይሰብራል” ብለዋል።

“የሞቱትንም ይሁን በሕይወት ያሉትን ዜጎቻችንን እናስመልሳለን” ሲሉ አክለዋል።

የእስራኤል ወታደሮች በአንድ ምሽት ባካሄዱት ኦፕሬሽን አስክሬኖቹን ማግኘት እንደተቻለ መከላከያው አስታውቋል።

ያገኘውን መረጃ ተከትሎ በጋዛ የተያዙ “አሸባሪዎችን በግዴታ በመጠየቅ” እንደደረሰበትም አክሏል።

አስክሬናቸው ወደ ጋዛ ከመወሰዱ በፊት ጥቃቱ በተፈጸመበት ኖቫ ፌስቲቫል አቅራቢያ እንደተገደሉ የወጣው መረጃ ይጠቁማል።

በፌስቲቫሉ ከ360 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

125 ታጋቾች የት እንዳሉ እስካሁን አልታወቀም።

የታጋቾች ቤተሰቦች ፎረም በሚል ንቅናቄ እያደረገ ያለው ቡድን የሦስቱ ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “በሐዝን አንገታችንን ደፍተናል። ልባችንም ተሰብሯል። የተገደሉት በአሸባሪው ሐማስ ነው። የሟቾች መንፈስ ግን አብሮን ይኖራል” ብሏል።

ከወራት በፊት በሐማስና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት 105 ታጋቾች ተለቀዋል።

በምላሹም 240 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እርስ ቤቶች ተለቀዋል።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ እንዳለው ታጋቾች የሚለቀቁት “ለሕዝባችን ፍትሐዊ አማራጭ ሲቀርብ ነው”።

በካይሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ረዥም ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመች ባለው ጥቃት እስካሁን ከ35 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

ወደ 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚገጥማቸውና መጠለያን ጨምሮ ሌሎችም ድጋፎች እንደሚፈልጉ የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።