የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፡ የማንቸስተር ደርቢ እና ሌሎች የሊጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች ግምቶች

ታትሟል

ባለፈው ሲቲ ከዩናይትድ ሲገናኙ ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ በልበ-ሙሉነት ነበር ግጥሚያውን የረቱት። እሑድ ኢቲሃድ የሚካሄደውን ፍልሚያስ ማን በአሸናፊነት ያጠናቅቃል?

የቢቢሲ ስፖርት ተንታኝ ክሪስ ሱተን “ማንቸስተር ዩናይትድ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ድል ሲቀናው ነበር፤ ነገር ግን ሲቲ ያለበት ደረጃ ላይ አይደሉም” ይላል።

የዘንድሮውን ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች እየገመተ ያለው ሱተን፣ የማንቸስተር ደርቢን ጨምሮ ከቅዳሜ እስከ ሰኞ ያሉ ጨዋታዎች ግምቱን ጀባ ብሏል።

ቅዳሜ

ብሬንትፈርድ ከቼልሲ

ቼልሲ ባለፈው ቅዳሜ በካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ በሊቨርፑል ተረትቷል። ይህ ጨዋታውም ቀላል ይሆንላቸዋል ብዬ አልገምትም።

ብሬንትፈርድ በበኩሉ እንደ አምናው ያለ አቋም እያሳየን አይደለም። ካለፉት ስድስት የሊጉ ጨዋታዎች በአምስቱ ተረትቷል።

እና ይህን ጨዋታ ምን ብዬ ብገምት ይሻለኛል? ለብሬንትፈርድ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ እጅግ አስፈላጊው ነው። ምክንያት ከወራጅ ቀጣና በጥቂት ነጥብ ነው ርቀው የሚገኙት።

የቼልሲው አሠልጣኝ ማውሪሲዮ ፓቼቲኖ በክለቡ መቀጠል ከፈለጉ የያዝነውን የውድድር ዘመን ጠንካራ ሆነው ማጠናቀቅ አለባቸው።

ይህ ጨዋታ ከአቻ የተለየ ውጤት ይኖረዋል ብዬ አላስብም።

ግምት፡ 1 - 1

ኤቨርተን ከዌስት ሀም

ኤቨርተን ከወራት በፊት የተጣለበት የ10 ነጥብ ቅጣት ተቀንሶ 6 ሆኖለታል። ይህ ደግሞ ለዚህ ጨዋታ መነቃቃት ይሆነዋል።

ኤቨርተኖች ድል ካጣጣሙ ቆይተዋል። ቅጣቱ መስተካከሉ ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ቆርጠው እንዲገቡ ያደርጋቸዋል ብዬ አስባለሁ።

ከብራይተን ጋር የነበራቸውን ጨዋታ ማሸነፍ ይገባቸው ነበር።

ብራዚላዊው ሉካስ ፓኩዌታ ከጉዳት መመለሱ ለዌስት ሀም መልካም ዜና ነው።

ነገር ግን እኔ ኤቨርተን በሜዳው አደገኛ ቡድን ነው ብዬ ነው የማስበው። ለዚህ ነው ዌስት ሀም ያለምንም ነጥብ ይመለሳል የምለው።

ግምት፡ 1 - 0

ፉልሀም ከብራይተን

ብራይተን በዎልቭስ ተሸንሮ ከኤፍ ኤ ዋንጫ ውጪ መሆኑ አስደንቆኛል። ነገር ግን ዘንድሮ ወጥ አቋም አለማሳየቱ መርሳት የለብንም።

በዚያ ላይ ካሮ ሚቶማ መጎዳቱ ሌላ ደንቃራ ይሆንባቸዋል። ሁለት ጨዋታ በተከታታይ ማሸነፍ ብዙም ያልሆነላቸው ብራይተኖች ይህ ጨዋታ እንደሚከብዳቸው እገምታለሁ።

ለዚህ ነው የዚህ ጨዋታ ውጤት ወደ ፉልሀም ያደላል የምለው። ፉልሀም ባለፈው ሳምንት ወደ ኦልድ ትራፈርድ ተጉዞ የሚገባውን 3 ነጥብ ይዞ ተመልሷል።

ግምት፡ 2 - 1

ኒውካስል ከዎልቭስ

ምንም እንኳ ማቴውስ ኩንሀ ቢጎዳባበትም ዎልቭስ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መምጣቱን መመልከት ችያለሁ።

ኒውካስልም እንደ ዎልቭስ ለኤፍ ኤ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ደርሷል።

ሁሌም ኒውካስል በሜዳው ይረታል ብዬ ብገምትም በውጤቱ እያፈርኩ ነው። በሜዳው ያደረጋቸውን ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

አሠልጣኙ ኤዲ ሃው መንበራቸው ላይ መቆየት ከፈለገ ይህን መቀየር አለበት። ምንም እንኳ የመባረር ስጋት ባይኖርበትም የውድድር ዘመኑን በመልካም ውጤት ማጠንቀቅ ይገባዋል።

ዎልቭስ ለዚህ ጨዋታ ያንሳል ብዬ ባልገምት ውጤት ወደ ኒውካስል የምታደላ ይመስለኛል።

ግምት፡ 2 - 1

ኖቲንግሀም ከሊቨርፑል

የሊቨርፑል ታዳጊ ተጫዋቾች ከቼልሲ ጋር በነበረው ፍፃሜ ባሳዩት ብቃት ውዳሴ እየደረሳቸው ነው። በኤፍ ኤ ዋንጫም ሳውዝአምፕተንን ረትተዋል።

ሳምንቱ ለየርገን ክሎፕ ድንቅ ነው። የመጀመሪያውን ዋንጫ ከማግኘታቸው ባለፈ ሌላ ዋንጫ የማግኘት ተስፋቸውም ለምልሟል።

ሞሐመድ ሳላህ፣ ዶሞኒክ ስፖስዝላይ እና ዋታሩ ኤንዶ ወደ መልካም አቋማቸው ቢመለሱ ደግሞ ሊቨርፑልን ማቆም ከባድ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ፎረስት ከመውረድ አደጋ ነፃ ቢሆኑም፣ ነጥብ ሊቀንስባቸው እንደሚችል እየተወራ ነው። ይህ ደግሞ ስጋት ላይ የሚጥል ነው።

በያዝነው ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ድል የቀናው የኑኖ ኤስፔሪቶ ሳንቶ ቡድን ቅዳሜ ዕለት ድል ይቀናዋል የሚል ግምት የለኝም።

ግምት፡ 0 - 2

ቶተንሀም ከክሪስታል ፓላስ

ቶተንሀም አሁንም በሚቀጥለው ዓመት በቻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የሚያስፈልገውን ነጥብ እያሳደደ ነው።

አሠልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ በዚህ ፍጥነት እስከ አራተኛ ለመውጣት ይፋለማሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር። ነገር ግን ቡድኑ በያዝነው የውድድር ዘመን ምርጥ ብቃቱን እያሳየን ነው።

አዲሱ የክሪስታል ፓላስ አሠልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር፤ በርንሊን በመርታት ሥራውን በሦስት ነጥብ ጀምሯል። ነገር ግን ይህ ጨዋታ ይከብደዋል።

ምንም እንኳ ስፐርስ ባለፉት ሳምንታት ነጥብ ሲጥል ብንመለከትም ከፓላስ የተሻሉ ተጫዋቾችን ይዟል።

ግምት፡ 3 - 0

ሉተን ከአስተን ቪላ

ሉተን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ባሳየው ብቃት ውዳሴ ተችሮታል። ሉተን በፕሪሚዬር ሊጉ የሚቆይ ከሆነ አሠልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ የውድድር ዓመቱ ምርጥ አሠልጣኝ መባል አለበት ብዬ ከዚህ ቀደም ተናግሪያለሁ።

ነገር ግን ኤቨርተን የተቀነሰበትን ነጥብ መልሶ ማግኘቱ እና ሉተን ያለፉትን ተከታታይ ጨዋታዎች መሸነፉ ስጋት ላይ የሚጥል ነው።

የአስተን ቪላ ተጫዋቾች ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ አቅጣጫ ሲያመሩ ያስፈራሉ። ነገር ግን ይህ የራሱ ጉዳት አለው።

ሉተን ጎል ያስቆጥራል ብዬ ባምንም ቪላ ነጥቡን ያገኛል ነው ግምቴ።

ግምት፡ 1 - 3

እሑድ

በርንሊ ከቦርንመዝ

በርንሊ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አለበት ማለት ከጀመርኩ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት 11 ነጥብ ያስፈልገዋል። የቀረው ደግሞ 12 ጨዋታ ነው። በውድድር ዘመኑ ሦስት ጊዜ ብቻ ነው ድል የቀናቸው።

ከኋላ ኳስ መሥርተው ለመጫወት የሚያደርጉት መኩራ ኪሳራ እያመጣባቸው ነው።

ቦርንመዝም እንዲሁ ምርጥ አቋም ላይ አይደሉም። የዶሚኒክ ሶላንኬ መጎዳት ደግሞ ሌላ ደንቃራ ነው። ቢሆንም በበርንሊ ይረታሉ ብዬ አልገምትም።

ግምት፡ 1 - 1

ማንቸስተር ሲቲ ከማንቸስተር ዩናይትድ

ዩናይትድ በኤፍ ኤ ዋንጫ ከኖቲንግሀም ሲጫወት ያሳየው ብቃት ሲቲን የሚያስጨንቅ አይደለም። ምንም እንኳ ያገኙት ድል ለአሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የራስመስ ሆይለንድ መጎዳት ሌላ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።

ማርከስ ራሽፈርድ የቀደመ አቋሙን ካሳየን ቆይቷል። ነገር ግን ኤሪክ ቴን ሀግ ሲቲን ለመርታት የሚሆን የተለየ ታክቲክ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ሲቲ ይህን ጨዋታ እንደሚረታ ምንም ጥርጥር የለኝም። ጥያቄው በምን ያህል የጎል ልዩነት የሚለው ነው።

ግምት፡ 6 - 1

ሰኞ

ሼፊልድ ዩናይትድ ከአርሰናል

አርሰናል በፕሪሚዬር ሊጉ የሚያደርገውን ጨዋታ በጎል በመንበሽበሽ እየረታ ይገኛል። ልክ እንደ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ መጣል የሚባል ነገር አአምሯቸው ላይ ሊመጣ አይገባም።

ባለፈው ሼፊልድ ወደ ኤሜሬትስ ስታድየም አቅንቶ 5 ለምንም ተረትቶ ተመልሷል። በወቅቱ ኤዲ ኒኬታህ ሦስት ጎል አስቆጥሮ ነበር።

ሼፊልድ ከአርሰናል ጋር አንገት ለአንገት ይተናነቃል ብዬ አላስብም። ባይሆን አርሰናል ጎል እንዳያገባ ለመከላከል ቆርጠው የሚገቡ ይመስለኛል።

መድፈኞቹ ቀድመው ጎል የሚያስቆጥሩ ከሆነ ለሼፊልድ አደጋ ነው የሚሆነው።

ግምት፡ 0 - 3