ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ኤርዶሃን ለንግግር ኢራን ገቡ

ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጋር ለመነጋገር ኢራን ገቡ።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው የካቲት ወር በዩክሬን ላይ ሠራዊታቸውን ካዘመቱ በኋላ ወደ ኢራን ሲጓዙ ይህ ሁለተኛው የውጭ ጉዟቸው ሆኗል።

ፑቲን እና ኤርዶሃን በኢራን ቆይታቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ እና የአገሪቱን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒን ያገኛሉ ተብሏል።

የእህል ምርት ገበያ፣ ሶሪያ እና ዩክሬን ፑቲን በቴህራን በሚያደርጉት ጉብኝት ላይ መነጋገሪያ ጉዳዮች እንደሚሆኑ አንድ የቱርክ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ከጦርነቱ በኋላ ከአገር ውጪ የሚያደርጉት ጉብኝት በቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አገራት ተወስኖ ቆይቷል።

ከአንድ ወር በፊት ፑቲን የቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አካል ወደነበሩት እና በአሁኑ ወቅት የሩሲያ አጋር በሆኑት በታጃኪስታን እና በቱርክሜንስታን ጉብኝት አድርገው ነበር።

የዛሬው የፑቲን ጉብኝት ልክ እንደ ሩሲያ ሁሉ በምዕራባውያን ማዕቀብ ስር ከምትገኘው ኢራን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት የሚያጠናክሩበት ይሆናል ተብሏል።

ይህ የፑቲን የኢራን ጉብኝት የተሰማው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ቴህራን ለሞስኮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን [ድሮኖች] ለማቅረብ በዕቅድ ላይ ናት ማለታቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

ዛሬ የሩሲያው ግዙፍ የኃይል ተቋም ጋዝፕሮም ከእስራኤል መንግሥት የነዳጅ ኩባንያ ጋር 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስምምነት ተፈራርሟል።

የፑቲንን የኢራን ጉብኝት በማስመልከት የፕሬዝዳንቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ በሰጡት መግለጫ ጉብኝቱ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ፑቲን ከአያቶላህ አሊ ኻሚኒ ጋር መገናኘታቸው “በጣም ጠቃሚ ነው” ያሉት አማካሪው፤ ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መተማመን ላይ የተመሠረተ ንግግራቸው ዳብሯል ብለዋል።

ምንም እንኳ ቱርክ እና ሩሲያ በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉ ቡድኖችን በየፊናቸው እየደገፉ የቆዩ ቢሆንም፤ በቅርብ ወራት ግን በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ጥረት እያደረጉ ነው።

የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ምዕራባውያን በሞስኮ ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀቦችን ሲጥሉ፤ አንካራ ግን የሩሲያ እና ዩክሬን አሸማጋይ ለመሆን ስትጥር እንጂ ሞስኮ ላይ ማዕቀብ ስትጥል አልታየችም።

ይሁን እንጂ ቱርክ በቅርቡ በሰሜን ሶሪያ የሚንቀሳቀሱትን እና በአሜሪካ የሚደገፉትን የኩርድ ታጣቂዎች ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት ዝታለች።

ይህን የቱርክ ዛቻ ሞስኮ እና ቴህራን በበጎ አልተመለከቱትም።

ኤርዶሃን ይህን ኦፕሬሽን ለማካሄድ ያቀዱት ከሶሪያ በሚያዋስናቸው የድንበር አካባቢ 30 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ደኅንነቱ የተረጋገጠ አካባቢን የመፍጠር እቅዳቸውን እውን ለማድረግ ነው።

ከፑቲን እና ኤርዶሃን ንግግር በኋላ በዩክሬን ወደብ ላይ የሚገኘው 22 ሚሊዮን ቶን እህል ወደ ሌላ አገር እንዲሄድ ጦርነት ውስጥ የገቡት የሩሲያ እና ዩክሬን መሪዎች ከስምምነት እንዲደርሱ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ ያሰማራቻቸው መርከቦች ምንም አይነት ጭነቶች ከዩክሬን እንዳይወጡ እና ወደ ዩክሬን እንዳይገቡ እያደረጉ ይገኛሉ።