ኔትፍሊክስ 'እስላማዊ እሴቶችን' የሚጥሱ ፊልሞቹን እንዲያነሳ ሳዑዲ አስጠነቀቀች

የኔትፊሊክስ ሎጎ እና ሪሞት የያዘ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ የገልፍ አገራት ኔትፍሊክስ እስላማዊ እና ማኅበራዊ መርሆችን የሚጥስ ይዘት ያላቸውን ፊልሞቹን እንዲያነሳ መጠየቃቸውን ተዘገበ።

ለሕጻናት የተዘጋጀውን ጨምሮ በቅርብ ጊዜ የተዘጋጀው ፊልም ሕግን የሚጥስ ነው ሲሉ ሳዑዲ እና የገልፍ አገራት ሚዲያ ተቆጣጣሪዎች አስጠንቅቀዋል።

ይሁን እንጂ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም።

ነገር ግን የሳዑዲ የመንግሥት ቴሌቪዥን፣ ኔትፍሊክስ ላይ ከተላለፉ የካርቱን ተከታታይ ፊልሞች ‘ጁራሲክ ዎርልድ ካምፕ ክሬታሴዎስ’ ላይ የተወሰዱ የተንቀሳቃሽ ምስል ቅንጭብጫቢዎችን አደብዝዞ አሳይቷል።

በተከታታይ የአኒሜሽን ፊልሙ ላይ ሁለት በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴት ህጻናት ፍቅራቸውን ሲገላለጹ እና ሲሳሳሙ ያሳያል።

አወዛጋቢው የፈረንሳይ ፊልም ‘ኪዩቲስ’ ም በአል ኢኽባሪያ ዘገባ ውስጥ እንደ ተጨማሪ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል። ዘገባው ኔትፍሊክስን “የህጻናትን ጤናማ አስተዳደግ አደጋ ላይ የሚጥሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸው መልዕክቶችን የሚያሳይ የፊልም ሽፋን” ሲል ከሷል።

ተቀማጭነቱን በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ያደረገው አል ኢኽባሪያ ቴሌቪዥን፤ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው ሌላ ቪዲዮም የኔትፍሊክስ የሥርጭት አገልግሎት “በግብረ ሶዶማውያን ላይ ከመጠን በላይ በማተኮር የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚያበረታታ ነው” ሲል ክሱን አቅርቧል።

ከዚህም ባሻገር የቴሌቪዥን ጣቢያው ተመሳሳይ ክስ ያላቸው በርካታ ታዋቂ ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገ ሲሆን ባለሥልጣናት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱም ጥሪ አቅርቧል።  

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሳዑዲ ኦዲዮ ቪዡዋል ሚዲያ ጀነራል ኮሚሽን እና የገልፍ ኮኦፕሬሽን ካውንስል የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ባለሥልጣናት በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ በህጻናት ላይ የሚሰሩትን ጨምሮ የማኅበረሰቡን ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ እሴት የሚጥሱ ይዘት ያላቸውን ፊልሞቹን እንዲያነሳ እና ሕግ እንዲያከብር ኔትፍሊክስን ማነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ባለሥልጣናቱ አክለውም መመሪያዎቹን አክብረው ጉዳዩን እንደሚከታተሉ እና ኔትፍሊክስ መሰል ፊልሞችንና ፕሮግራሞችን ማሰራጨቱን ከቀጠለ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

ይህንን ክስ በተመለከተ ከኔትፍሊክስ እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

በሱኒ ሙስሊሞች የምትመራው ሳዑዲ አረቢያ፣ በጾታዊ ጉዳዮች፣ ጾታዊ ምንነትን የተመለከተ ሕግ ባይኖራትም፣ የተመሳሳይ ጾታ ወሲባዊ ግንኙነትን ጨምሮ ከትዳር ውጭ ያለ ጾታዊ ግንኙነት በጥብቅ የተከለከለ ነው።

በአገሪቷ እስላማዊ ሕግ ትርጓሜ መሠረት በስምምነት የተደረገ የተመሳሳይ ጾታ ወሲባዊ ግንኙነት እንደ ድርጊቱ ሁኔታ በሞት አሊያም በግርፋት ያስቀጣል።

ሚያዝያ ወር ላይ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ሲኒማ ቤቶች፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚያመለክቱ ይዘቶች ተቆርጠው እንዲወጡ ያቀረቡትን ጥያቄ የፊልሙ አከፋፋይ ዲዝኒ ስቱዲዮ ውድቅ ካደረገ በኋላ ‘ዶክተር ስትሬንጅ ኢን ዘ መልቲ ቨርስ ኦፍ ማድነስ’ የሚለውን ፊልም ሳያሳዩ ቀርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሰዎች ሲሳሳሙ የሚያሳየው አኒሜሽን ፊልም ‘ላይትይር’ ሰኔ ወር ላይ በሳዑዲ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ታግዷል ተብሏል።

ባለፈው ወርም ዩቲዩብ እስላማዊ እሴቶችን የሚጥሱ ተገቢ ያልሆኑ ማስታወቂያዎችን ፈቅዷል በሚል በሳዑዲ ባለሥልጣናት ክስ ቀርቦበታል።