ከሞሮኮ የተነሱት ስደተኞች በፈጠረው ውዝግብ፣ ስፔን የጣልያን ድንበር ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ወሰነች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአውሮፓ አገራት በሆኑት ስፔን እና ጣልያን መካከል የተፈጠረው ውዝግብ መካረሩን ተከትሎ፤ ስፔን ከጣልያን በሚነሱ ሁሉም የአየር እና የባሕር ጉዞዎች ላይ የድንበር ቁጥጥር እንዲደረግ ወሰነች።

ከትናንት አርብ አንስቶ መተግበር የጀመረው ይህ የቁጥጥር እርምጃ፣ ለአንድ ወር እንደሚቆይ ተገልጿል።

ስፔን ውሳኔውን ያሳለፈችው፣ ከሞሮኮ የተነሱ 78,000 ገደማ ስደተኞች የአገሪቱ ግዛት ወደሆነችው ሴኡታ መግባታቸውን ተከትሎ ጣልያን ተመሳሳይ ገደቦችን ከጣለች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

ስፔን በጣልያን የተጣለው የቁጥጥር እርምጃ እስከ እሁድ ድረስ እንዲነሳ ጠይቃለች።

ጣልያን ግን እስከሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ "አዲስ የስደተኞች ማዕበል" ወደ ሴኡታ ይመጣል ብላ እንደምትጠብቅ አስታውቃለች። በዚህም የተነሳ ቁጥጥሩ እንደሚቀጥል ገልጻለች።

በሴኡታ የተፈጠረው ቀውስ የስፔኑን ሶሻሊስት መሪ ፔድሮ ሳንቼዝ እና የአውሮፓ ኅብረት የስደተኞች ሕጉን እንዲያጠብቅ ለረጅም ጊዜ ሲሞግቱ የነበሩትን የጣልያኗ ወግ አጥባቂ መሪ ጆርጂያ ሜሎኒን ፍጥጫ ውስጥ ከትቷል።

ጣልያን ከስፔን ጋር የምትጋራው የመሬት ድንበር የላትም። የጣልያን መንግሥት ባለፈው ሳምንት ላይ፣ በአውሮፓ አገራት መከካል ነፃ የድንበር እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚያደርገው የሸንገን ስምምነት ለጊዜው እንዲታገድ ወስናለች።

ይህ የሮም ውሳኔ፣ ሴኡታ የገቡት ስደተኞች ወደ ጣልያን እንዳይሻገሩ ለመከላከል ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

ማድሪድ ግን ውሳኔው "በሐሰተኛ ክርክር" ላይ የተመሠረተ እንደሆነ በመግለጽ ውሳኔውን ተቃውማዋለች። ሰሜን አፍሪካ ውስጥ ወደምትገኘው የስፔን ግዛት ሴኡታ የገቡት ስደተኞች የሸንገን አሰራር ወደሚተገበርበት አካባቢ የሚገቡበት መንገድ እንደሌለም አስረድታለች።

ስፔን አርብ ዕለት ላሰማችው ማስጠንቀቂያ ምላሽ የሰጠው የጣልያን መንግሥት በአገሪቱ የተቀመጠውን "ቀነ ገደብ" እንደማይቀበል አስታውቋል።

"ጣልያን ላይ የሚጋረጡ የደኅንነት እና የሽብር ስጋቶች ሙሉ በሙሉ እስካልተወገዱ ቢያንስ እስከ ነሐሴ 9 ድረስ፣ ከስፔን ለሚመጡ የሶስተኛ ሀገር ዜጎች የሸንገን ስምምነት ተፈጻሚነት እንዲታገድ የተላለፈውን ውሳኔ በምንም አይነት ሁኔታ በድጋሚ እደማታጤን" የአገሪቱ መንግሥት ገልጿል።

ድንበር ላይ ቁጥጥር የሚያደርጉ ባለሙያዎች ከስፔን ወደ ጣልያን የሚመጡ የስፔን እና የሌሎች የአውሮፓ አገራት ዜጎች በተቻለው መጠን ምቾት እንዲሰማቸው "የሚችሉትን ሁሉ" እያደረጉ መሆኑን የሮም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ወደ ጣልያን የሚገቡ የስፔን ዜጎች ተጨማሪ ቁጥጥር እንደማይደረግባቸው እና ይህ አይነቱ እርምጃ የሚወሰደው የአውሮፓ ህብረት አባል ያልሆኑ አገራት ዜጎች ላይ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል።

ነገር ግን ባለፉት ቀናት በጣልያን በሚገኙ በርካታ የአየር ማረፊያዎች ውስጥ ረጅም ሰልፎች መታየቱት እና ከስፔን የመጡ መንገደኞች ለብቻው ወደተዘጋጀ የቁጥጥር መስመር መወሰዳቸው ተዘግቧል።

ስፔን የወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ጣሊያናውያን መንገደኞች እንዲሁም የሌሎች አገራት ዜጎች ሆነው ከጣልያን የተነሱ ጎብኚዎች ላይ ፓስፖርት፣ ዜግነት እና ቪዛ ቁጥጥር እንዲካሄድባቸው ያደርጋል።

"ውሳኔው እንዲተላለፍ ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎች እስካልተለወጡ ድረስ" እርምጃው እስከ መስከረም ይቆያል ተብሏል።