ከኢላን መስክ ጋር የቃላት ምልልስ ውስጥ የገቡት የቬኔዙዌላው ፕሬዝዳንት ኤክስን አገዱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከቢሊየነሩ ኢላን መስክ ጋር በአደባባይ የቃላት ምልልስ ውስጥ የገቡት የቬኔዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ኤክስን ለ10 ቀናት አገዱ።

የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ ፕሬዝዳንቱን “አምባገነን” እንዲሁም “ቁምነገር አልባ” ሲል ከመወረፍ አልፎ የፕሬዝዳንቱን የማሰላሰል አቅም ከአህያ ጋር አነጻጽሯል።

ፕሬዝዳንቱ በምላሹ መስክን፤ ‘ፋሽስት’ እንዲሁም በቬኔዙዌላ “ጥላቻ የሚዘራ እና የእርስ በእርስ ጦርነት የሚቀሰቅስ” ሲሉ ወርፈውታል።

የሁለቱ ግለሰቦች ውዝግብ የጀመረው አወዛጋቢው የቬኔዙዌላን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኒኮላስ ማዱሮ ማሸነፋቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተደረገው ምርጫ በብዙ የምርጫ ታዛቢዎች ዴሞክራሲያዊ አልነበረም ተብሏል።

ከአንድ ወር በፊት የተደረገውን የምርጫ ውጤት ያልተቀበሉ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ጸረ-መንግሥት የሆኑ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ምርጫውን ማሸነፋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አለን ሲሉ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ማዱሮ የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት የሳይበር ጥቃት ደርሶበት ነበር ካሉ በኋላ፤ ኢላን መስክ ዳግም እንዳልመረጥ የሳይበር ጥቃት አስከፍቶብኛል ብለዋል።

በቬኔዙዌላ መንግሥት ምርጫውን እንዲታዘብ ወደ አገሪቱ የገባው የካርተር ማዕከል ግን በምርጫ ቦርዱ ላይ የሳይበር ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት አልታየም ብሏል።

ማዱሮ በቴሌቪዥን መስኮት በቀጥታ በተላለፈ ንግግራቸው ለኢላን መስክ ምላሽ ለመስጠት በሚመስል እርምጃ ኤክስ ለ10 ቀናት በቬኔዙዌላ ይታገዳል ብለዋል።

“ኢላን መስክ የኤክስ ባለቤት ነው። ሁሉንም ሕጎች ጥሷል” ብለዋል ማዱሮ።

“ጥላቻ በመንዛት፣ በፋሺዝም፣ የእርስ በእርስ ጦርነት በመቀስቀስ፣ ለቬኔዙዌላዊያኖች ሞት በመመኘት ሁሉም ሕጎች ጥሷል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው።

ከቬኔዙዌላው ምርጫ በፊት ኢላን መስክ ለዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ እጩ ድጋፉን ገልጾ ነበር።

ከምርጫው በኋላ መስክ “በማዱሮ መንግሥት ትልቅ የምርጫ ውጤት ማጭበርበር ተከናውኗል፤ አምባገነኑ ማዱሮ አሳፋሪ ናቸው” ሲል ጽፎ ነበር።

በዚህ ያልተገደበው መስክ፤ የፕሬዝደንት ማዱሮን የማሰላሰል አቅም ከአህያ ጋር በማመሳሰል "የቬንዙዌላ ሕዝብ ይህን ቁም-ነገር አልባ ሰው በቃን ያሉበት ጊዜ ነው" ብሏል።

የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ማዱሮ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ይፋ ቢያደርግም የአሜሪካ፣ አርጀንቲና፣ ኡራጉዋይ እና ኢኳዶር መንግሥታት ምርጫውን ያሸነፉት ተቃዋሚው ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ ናቸው ብለዋል።

ምርጫ ታዛቢው የካርታር ማዕከል እንዲሁም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ አይደለም በማለት ዴሞክራሲያዊ አይደለም ሲል ደምድሟል።