በእስራኤል እስር ቤት ያሉ ፍልስጥኤማውያን እስረኞች የረሃብ አድማ ሊመቱ ነው

ታትሟል

በእስራኤል እስር ቤት ያሉ ፍልስጥኤማውያን እስረኞች በጅምላ የረሃብ አድማ ሊመቱ መሆኑን የፍልስጥኤም የዜና አገልግሎት አስታወቀ።

ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ እስረኞች የእስር ቤቱን ሁኔታ በመቃወምም ነው የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉ ባለስልጣናቱ የተናገሩት።

ዋፋ የዜና ወኪል እንደገለጸው እስር ቤቱ የታሳሪዎችን ይሻሻል ጥያቄ አሻፈረኝ እንዳለም ዘግቧል።  በዚህ ጉዳይ የእስራኤል ባለስልጣናት የሰጡት አስተያየት የለም።

እስራኤል ባለፈው ዓመት እስር ቤት ተሰብሮ እስረኞች ካመለጡ በኋላ እስራኤል በእስረኞች አያያዝ ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እየወሰደች ነው ተብሏል።

ከከፍተኛ ጥበቃ እስር ቤት ያመለጡ ስድስት ፍልስጥኤማውያን ጉዳይ ለእስራኤል ባለስልጣናት አሳፋሪ ሁኔታን ፈጥሯል።

እነዚህ ያመለጡት እስረኞች ሁለት ሳምንታት በሚጠጋ ወቅትም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የፍልስጥኤም የእስረኞች እና የቀድሞ እስረኞች ባለስልጣን ኮሚቴ ተወካዮች የረሃብ አድማውን “ጥያቄውን ማሳካት ከቻለ በኋላ እንዲቆም መወሰኑን” ዋፋ ዘግቧል።

የረሃብ አድማው የሚቆመው የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አካላት እንፈፅማለን ያሉትን በማሟላት ላይ የተመሰረተ ነው ብሏል። 

የፍልስጥኤም እስረኞች የእስራኤል ባለስልጣናት ሁኔታቸውን እንዲያሻሽሉ ግፊት ለማድረግ የረሃብ አድማን እንደ ስልት ለአመታት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

ከነዚህም መካከል በታህሳስ ወር በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ካሊል አዋውዴህ ከታሰረበት ጀምሮ ለስድስ ወራት ያህል በረሃብ አድማ ላይ የነበረ ሲሆን በዚህ ሳምንት ረቡዕም አድማውን አቁሟል።

በጥቅምት ወር የእስራኤል ባለስልጣናት እንደሚፈቱት ቃል እንደገቡለትም ተናግሯል።

በእስራኤል እስር ቤት ያሉ የፍልጥኤማውያን እስረኞች ጉዳይ የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበው የፍልስጥኤምን ህዝብ አንድ ያደረገ ነው።

ፍልስጤማውያን በእስራኤል የታሰሩ ፍልስጥኤማውያን እስረኞችን  እንደ የፖለቲካ እስረኞች ይቆጥሯቸዋል።

በርካታዎቹ በደህንነት ወንጀሎች፣ በሽብርተኝነት እና በግድያ ወንጀል በእስር ተፈርዶባቸው በእስር ቤት ይገኛሉ።

በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ 4 ሺህ 500 ፍልስጥኤማውያን እንዳሉ የፍልስጥኤም ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ከመካከላቸው 700 ያህሉ ያለ ፍርድ እና ክስ አስተዳደራዊ እስር ተብሎ በሚታወቅ ሁኔታ በእስር ላይ ናቸው።