እስራኤል ከአሜሪካ የተሰጣትን ጦር መሣሪያ 'ኢ-ሰብአዊ' ድርጊት ሳትፈጽምበት እንዳልቀረ አሜሪካ ስጋቷን ገለጸች

ታትሟል

አሜሪካ ለእስራኤል የሰጠሁት ጦር መሣሪያ በጋዛ 'ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግን በጣሰ መንገድ' ላልተገባ ተግባር ሳይውል አልቀረም ስትል ስጋቷን ገለጸች።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው አንድ ሰነድ ለእስራኤል የተሰጡት ጦር መሣሪያዎች በምን መንገድ እንደዋሉ ለመፈተሽ የሞከረ ነበር።

ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ እንደሚጠረጥረው በነዚህ ከአሜሪካ በተለገሱ ጦር መሣሪያዎች በጋዛ ላይ የተወሰኑ ሰብአዊ ጥሰቶች ሳይፈጸሙ አልቀረም።

ሆኖም በዚህ ረገድ 'የአሜሪካ መንግሥት ሙሉ መረጃ የለውም' ብሏል ሰነዱ።

ይህ ሪፖርት ለኮንግረስ የቀረበው ዐርብ ዕለት ነበር። ዋይት ሐውስ ለእስራኤል የተሰጡት ጦር መሣሪያዎች የዋሉበት አግባብነት እንዲጣራ ጥያቄ አቅርቧል።

ምንም እንኳ የአሜሪካ መንግሥት በነገሩ አሳሳቢነት መግለጫ ቢያወጣም በትክክል የእስራኤል ጦር መሣሪያዎቹን ያዋለው በጋዛ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ ነው ብሎ አፉን ሞልቶ ለመናገር ግን አልደረፈረም።

የሰነዱ መግለጫ እንደሚለው እስራኤል እጅግ ፈታኝ ወታደራዊ ፈተና ከሐማስ ገጥሟት እንደነበር ያወሳል።

ይህን ተከትሎ እስራኤል መሣሪያዎቹን በአግባቡ ለመጠቀም የገባችው ቃል መጀመርያ አካባቢ እምነት የሚጣልበት ነበር ካለ በኋላ ይህን ተከትሎ ጦር መሣሪያዎቹ ወደ እስራኤል እንደተላኩ ያትታል።

ሰነዱ እንደሚለው ሐማስ ንጹሐንን ጋሻ ስለሚያደርግ እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ስታደርግ የትኛው ነው ወታደራዊ ቀጠና የሚለውን ለመወሰን መሬት ላይ አስቸጋሪ ሳይሆንባት እንዳልቀረ ይተነትናል።

ያም ሆኖ እስራኤል ከአሜሪካ የተሰጣትን ጦር መሣሪያ ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ መልኩ ንጹሐን ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ ሳትጠቀም እንዳልቀረ ግምት እንወስዳለን ይላል ሰነዱ።

ሰነዱ ጨምሮ፣ እስራኤል ጦር መሣሪያዎቹን በተገቢውና ሕጋዊ መንገድ ለመጠቀም ልምዱም እውቀቱም አስፈላጊ ቁሳቁሶችም ያሏት ሆኖ ነገር ግን ሰላማዊ ዜጎችን ሞት ለመቀነስ ምናልባት ሁሉንም አስፈላጊ ጥንቃቄዎች አላደረገች እንደሆነ ይጠቁማል። ይህም እንዲባል ያስቻለው መሬት ላይ የበዛ የንጹሐን ግድያ በመታየቱ ነው።

ሪፖርቱ እንዳለው የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ሰብአዊ ድርጅቶች የእስራኤልን ሰብአዊ ጉዳትን ለመቀነስ ያደረገችው ጥረት ‘ያልተሳካ፣ በቂ ያልሆነና ወጥነት የሌለው” ነበር።

በመጨረሻም ሰነዱ የአሜሪካ መንግሥት እስራኤል ሰብአዊ ጥፋትን ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር በቂ ትብብር እንዳላደረገች አንስቶ ይወቅሳል።

ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍም ለማድረስ በመጀመርያዎቹ የግጭት ወራት ከእስራኤል የታየው ተባባሪነት ዝቅተኛ ነበር ብሏል።

ይህን ሪፖርት ካሰናዱት አንዱ የሆነት በቱርክ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሳተርፊልድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እንዲህ ዓይነቱ ሪፖርት ከአሜሪካ በእስራኤል ላይ ሲወጣ በዐይነቱ የመጀመርያው ነው።

ይህም አሜሪካ በእስራኤል የሚፈጸሙ ደርጊቶችን በቀጣይነት እንድታጤን ያደርጋታል።

ይህ ሪፖርት የወጣው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በይፋ እስራኤል በራፋህ አዲስ ዘመቻ የምትከፍት ከሆነ አንዳንድ የጦር መሣሪያዎችን ላንልክ እንችላለን ከማለታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

ይህ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ የእራኤሉ ፕሬዝዳንት ቤኒያሚን ናታንያሁ ዘመቻውን ''ብቻችንም ቢሆን እንወጣዋለን'' ብለው መዛታቸው አይዘነጋም።

እንደዛቱትም በራፋህ በከፈቱት ዘመቻ ከሰኞ ወዲህ ብቻ ከ80ሺህ በላይ የራፋህ ነዋሪዎች ተሰደዋል።

የእስራኤል ወታደሮች መጠነኛና የተጠና ዘመቻ ነው ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት በራፋህ ላይ ከመክፈታቸው በፊት ከግብጽ ወደ ራፋህ የሚወስደውን ቁልፍ መንገድ በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

ይህ ጎዳና በተለይ ለሰአብአዊ ድጋፍ ማስተላለፊያ ወሳኝ የሚባል በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ስጋት ገብቶኛል ብሏል።

እስራኤል የሐማስን መብረቃዊ ጥቃት ተከትሎ ድርጅቱን አጠፋለሁ ብላ በመነሳት ከሰባት ወራት በፊት በከፈተችው ዘመቻ በትንሹ 34ሺህ 900 በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደሚለው ከሆነ ከነዚህ ሟቾች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕጻናትና ሴቶች ናቸው።