በሲሪላንካ የተከሰተውን ህዝባዊ አለመረጋጋት ተከትሎ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ቃለ መኃላ ፈጸሙ

ታትሟል

ሲሪላንካ በምጣኔ ኃብት ቀውስና አለመረጋጋት እየተናጠች ባለችበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክሬሜሲንግ በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት ቃለ መኃላ ፈጸሙ።

ተጠባባቂው ፕሬዚዳንት በጦር አውሮፕላን ከአገራቸው የኮበለሉትን ጎታባያ ራጃፓክሳን ይተካሉ።

በአገሪቷ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተቃዋሚዎች የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ጥሰው ከገቡ በኋላ ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን ጥለው ወጥተዋል።

የፕሬዚዳንቱን ከስልጣን መልቀቅ ከተሰማ በኋላ ተቃዋሚዎች በአገሪቱ የተጣለውን የሰዓት እላፊ አዋጅ በመጣስ ደስታቸውን ሲገልጹም ታይተዋል።

ሲሪላንካ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተናጠች ሲሆን በአገሪቱ በ70 ዓመታት ውስጥ ያልታየ በተባለው አስከፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድኃኒት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየታገለች ነው

ፓርላማው አዲስ ፕሬዚዳንት የመምረጥ ሂደቱን በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ የሚጀምር ሲሆን የፓርላማ አባላቱም በአንድ ሳምንት ውስጥ ድምፃቸውን እንደሚሰጡም ይጠበቃል።

ገዥው ፓርቲ በፓርላማው ውስጥ አብላጫ ወንበሮችን የተቆጣጠረ ከመሆኑ አንፃር የፓርላማ አባላቱ ከራጃፓክሳ ቤተሰብ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክሬሜሲንግን ይደግፋሉ ተብሎ ይታሰባል።

ነገር ግን የሲሪላንካ ህዝብ ይህንን ይቀበላል ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክሬሜሲንግ ከስልጣን ይልቀቁ የተቃዋሚዎች ቁልፍ ጥያቄ ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ተቃዋሚዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ ጥሰው በመግባት ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል።

ማኑሪ ፓባሳሪ የተባለች ተቃዋሚ ለቢቢሲ እንደተናገረችው በአሁኑ ወቅት በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት ቃለ መሃላ በፈጸሙት ራኒል ዊክሪሜሲንጌ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ በሚቀጥሉት ቀናት ይጠበቃል።

“ባለስልጣኑ የህዝብ ድጋፍም ሆነ ለመምራት ፈቃድ የላቸውም ከዚህም በተጨማሪ የታወቁ የቀድሞው ፕሬዚዳነት ራጃፓክሳ ደጋፊ ናቸው” የምትለው ተቃዋሚዋ “"አዲሱ ፕሬዝዳንት እና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የራጃፓክሳ ደጋፊ መሆን የለባቸውም ማለቴ ነው።" ብላለች

የሲሪላንካ ማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪ ናንዳላል ዋይራሲንጌ በበኩላቸው በቅርቡ የተረጋጋ መንግስት ካልተቋቋመ ሃገሪቷ ቀጥ እንደምትል አስጠንቅቀዋል።