ናይጄሪያዊው ቢሊየነር የእንግሊዙን የእግር ኳስ ክለብ ለመግዛት ከጫፍ ደረሱ

ታትሟል

ናይጄሪያዊው ቢሊየነር ዶዚ ማሞቦውሲ በእንግሊዝ ሁለተኛ ሊግ እየተጫወት የሚገኘውን ሼፊልድ ዩናይትድ እግር ኳስ ክለብን ለመግዛት ከጫፍ ደረሱ።

የቻምፒዮንሺፕ ክለቡ ባለቤት የሆኑት የሳዑዲ ዜጋው ልዑል አብዱላህ በክለቡ ሽያጭ ዙሪያ ከናይጄሪያዊው ባለሃብት ጋር የመጨረሻ ንግግር እያደረጉ እንደሆነ ቢቢሲ ከምንጮች ተረድቷል።

ቲንጎ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዲዞ ማሞቦውሲ የዮርክሻየር እግር ኳስ ክለቡን ለመግዛት የተቃረቡት ከስምንት ወራት በፊት አሜሪካዊው ነጋዴ ሄነሪ ሞውሪስ ክለቡን ለመግዛት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ከቀረ በኋላ ነው።

በግብረና ቴክኖሎጂ እና ፋይናንስ ሥራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ናይጄሪያዊው ንብረታቸው 7.6 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

የ43 ዓመቱ አፍሪካዊ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ ከሼፊልድ ዩናይትድ ባለቤት እና ዳይሬክተር ይሁንታን የሚያገኙ ከሆነ በ108 ሚሊዮን ዶላር የክለቡ ባለቤት ሊሆኑ ይችላሉ።

አፍሪካውያን በእንግሊዝ የእግር ኳስ ክለቦች ውስጥ

ናይጄሪያዊው ባለሃብት የሼፊልድ ዩናይትድ ግዢን የሚያሳኩ ከሆነ የእንግሊዝ ከለብን ከዚህ ቀደም ከገዙ አፍሪካውያን ተርታ ያሰልፋቸዋል።

ከአፍሪካ የእንግሊዝ ክለቦችን በመግዛት አልያም በማስተዳደር ግብጻውያን ቀዳሚው ናቸው።

ግብጻዊው ናሲፍ ሳዊሪስ በፕሪሚየር ሊጉ የሚጫወተው አስተን ቪላ ፕሬዝዳንት እና ከክለቡ ባለቤቶች መካከል አንዱ ናቸው።

የሞሮኮ ዜጋ የሆኑት አብደላህ ሌምሳጋም ደግሞ ከእአአ 2018 እስከ 2022 ድረስ በእንግሊዝ አምስተኛ ሊግ የሚጫወተው አልድሃም አትሌቲክ ክለብ ባለቤት ነበሩ።

ትውልደ ደቡብ አፍሪካዊው ጌሪ ኦቶ ደግሞ በእንግሊዝ አራተኛ ሊግ የሚጫወተው ሱቶን ዩናይትድ ባለቤት መካከል አንዱ ናቸው።

ከጥቂት ወራት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው የግብጽ ተወላጅ የነበሩት አሴም አላም ደግሞ ሃል ሲቲን እአአ 2010 ገዝተው ነበር። አሴም አላም ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከማሳደጋቸው በፊት ለኤፍኤ ካፕ የዋንጫ ጨዋታ አድርሰውም ነበር።

ሞሐመድ አል-ፋዬድ የተባሉ ግብጻዊ ደግሞ እአአ 1997 ላይ ፉልሃምን በ30 ሚሊዮን ዶላር ገዝተው ነበር። ግብጻዊው ክለቡ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ወጪ በማድረግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማሳደግ ችለው ነበር።