የዶሚኒካን ሪፐብሊክ ሚኒስትር በባልንጀራቸው ተገደሉ  

ታትሟል

የዶሚኒካን ሪፐብሊክ የአካባቢና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር የነበሩት ሰው ቢሯቸው ውስጥ በሥራ ላይ ሳሉ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡

የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት የ55 ዓመቱ ሚኒስትር የተገደሉት አለኝታዬ በሚሉት የልጅነት ጓደኛቸው ነው፡፡

ሚኒስትር ኦርላንዶ ሜራ ይህ ክፉ ዕጣ ሲገጥማቸው በስብሰባ ላይ ነበሩ ተብሏል፡፡

በትንሹ ስድስት ጥይቶች ተተኩሶባቸው ነው የሞቱት ብለዋል፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት፡፡

የዶምኒካን ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ እንዳሉት ደግሞ ጥቃት ፈጻሚው ሚጉል ክሩዝ የሚባል የሟች የልጅነት ወዳጅና ባልንጀራ ነበር፡፡

አሁን በሕግ ቁጥጥር ሥር ነው ብለዋል፣ ቃል አቀባዩ፡፡

የሟቹ ሚኒስትር ቤተሰብ ባወጣው መግለጫ ልጃቸው በልጅነት ጓደኛቸው ቢገደሉም ገዳይን ይቅር ብለናል ብለዋል፡፡

‹‹ቤተሰቡ ይህን ገዳይ ይቅር ለእግዜር እንዳለው ለመግለጥ እንወዳለን፤ ምክንያቱም የልጃችን ኦርላንዶ አንድ በጎ ውርስ ጠላትን ይቅር ማለትና ቂም አለመያዝ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ኦርላንዶ ሜራ አሁን አገሪቱን የሚመሩት የፕሬዝዳንት ሉዊስ አቢናደርን አስተዳደር በመቀላቀል ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ በሥልጣን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

የሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ ፕሬዝዳንት አቢናደር ለሟች ቤተሰብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ሟቹ ሚኒስትር ኦርላንዶ ሜራ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሳልቫዶር ብላንኮ ልጅ ነበሩ፡፡

ሟቹ ሚኒስትር ኦርላንዶ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ፡፡

ባለቤታቸው በብራዚል የዶምኒካን ሪፐብሊክ አምባሳደር ናቸው፡፡