ልጁን ለማዳን ከጀልባ የዘለለው እንግሊዛዊ አስክሬን ጣልያን ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, ARAN CHADA/LINKEDIN
የልጁን ሕይወት ለማዳን ከጀልባ የዘለለው እንግሊዛዊ አስክሬኑ ጣልያን ተገኘ።
አረን ቻዳ የተባለው ግለሰቡ ልጁን ለመታደግ ከጀልባ ከዘለለ በኋላ ለሳምንታት ጠፍቶ ቆይቷል።
በስተመጨረሻ አስክሬኑ ጣልያን ተገኝቷል።
ጋርዳ የተባለ ባሕር አካባቢ ከትዳር አጋሩና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ባለፈው ወር እየተንሸራሸሩ ነበር።
የአረንን ልደት ለማክበር ነበር ሽርሽሩ የተዘጋጀው።
52 ዓመት ይሞላው ነበር።
ቤተሰቡ ጀልባ ተከራይቶ በባሕር እየተጓዘ ሳለ የአረን ልጅ ሊሞን የተባለ ሪዞርት አካባቢ ችግር ገጠመው።
አባት ልጁን ለማዳን ከጀልባው ከዘለለ በኋላ አስክሬኑ ከሊሞን በ800 ሜትር ርቀት፣ በ316 ሜትር ጥልቀት እንደተገኘ ነፍስ አዳኞች ገልጸዋል።
ልጁን ካዳነ በኋላ ውሃ ውስጥ ሰምጧል።
“የሰመጠው አንዳች ሕመም ስላለበት ይመስለኛል” ብሏል ነፍስ አዳኙ።
አረን ልጁን ካዳነ በኋላ እሱ መጥፋቱን መጀመሪያ ለነፍስ አዳኞች የገለጸው ቤተሰቡ ነበር።
አንድ የዐይን እማኝ “እናትየው ስትጮህ አባትየው ልጁን ለማዳን ዘሎ ባሕር ውስጥ ገባ” ብሏል።
መጀመሪያ በጀልባ አሰሳ ከተደረገ በኋላ፣ በሄሊኮፕተርና በነፍስ አዳኞች አማካይነት ፍለጋው ተካሂዷል።
ፖሊሶችና በጎ ፈቃደኞችም በአሰሳው ተባብረዋል።
የአካባቢው ባለሥልጣኖች “በሰሜን ጣልያን የሞተውን እንግሊዛዊ ቤተሰብ እየደገፍን ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, GUARDIA COSTIERA












