ዩክሬን ግዛቶቿ ወደ ሩሲያ መጠቃለላቸውን ተከትሎ በአስቸኳይ የኔቶ አባል ለመሆን ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አራት የዩክሬን ግዛቶች በሩሲያ ስር መጠቃለላቸውን ካወጁ በኋላ ዩክሬን በአስቸኳይ የኔቶ አባል ለመሆን ጥያቄ አቀረበች።
ሩሲያ ያካሄደችውን ወረራ ተከትሎ በቁጥጥሯ ስር ባስገባቻቸው አራት አካባቢዎች አጠያያቂ የሆነ ሕዝበ ውሳኔ ከቀናት በፊት ተካሂዶ ነበር።
ፑቲን ዛሬ አርብ ሞስኮ ውስጥ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ሉሃንስክ፣ ዶኔትስክ፣ ዛፖሪዢያ እና ኼርሶን የተባሉት የዩክሬን ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን አውጀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር በአራቱ ግዛቶች ውስጥ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ዜጎች “ምርጫቸውን” ያሳወቁበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዩክሬን የተወሰዱት ስፍራዎች ከዚህ በኋላ ለድርድር የማይቀርቡ የሩሲያ ግዛቶች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ፣ አገራት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስፈልጋቸው ሂደት ሳይጠበቅ አገራቸው በአስቸኳይ አባል እንድትሆን ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዜሌንስኪ አገራቸው የኔቶ አባል ለመሆን መመዘኛውን እንደምታሟላ በመጥቀስ “ዩክሬን በአፋጣኝ የኔቶ አባል እንድትሆን የሚቀርበውን ማመልከቻ በመፈረም ወሳን የሆነውን እርምጃ ወስደናል” ብለዋል።
ለሩሲያ ወረራ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛ የሆነው ዩክሬን የምዕራባውያኑን ወታደራዊ የትብብር ማኅበር የሆነውን ኔቶን የመቀላቀል ፍላጎት ነበር።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ሩሲያ የዩክሬንን ምሥራቃዊ ግዛቶችን ለመቆታጠር ብትጭልም ወደ ዋና ከተማዋ መግፋት ግን ሳትችል ቆይታለች። ከሳምንታት ወዲህ ደግሞ የዩክሬን ሠራዊት አንዳንድ ቦታዎችን መልሶ ለመቆጣጠር መቻሉ ተዘግቧል።
ሩሲያ ከዩክሬን በወረራ ከያዘቻቸው ግዛቶች መካከል ሉሃንስክ፣ ዶኔትስክ፣ ዛፖሪዢያ እና ኼርሶን በይፋ የሰፊ ግዛቷ አካል በማድረግ በማወጅ በይፋ ጠቅላቸዋለች።
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ፑቲን አራቱ ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ የፈረሙ ሲሆን፣ ለግዛቶቹ መሪዎችንም ሾመዋል።
ፑቲን ባደረጉት ንግግር ለጦርነቱ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአውሮፓ እና በመላው ዓለም ለተከሰተው ቀውስ ዩክሬንን እና የምዕራባውያንን ተጠያቂ አድርገዋል። ጨምረውም ዩክሬን “በአስቸኳይ ተኩስ አቁማ ወደ ድርድር እንድትመለስ” ጥሪ አቅርበዋል።
ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን መጠቅለልን ተከትሎ የተለያዩ አገራት ተቃውሟቸውን ከማሰመታቸው ባሻገር ተጨማሪ ዕቀባዎችንና እገዳዎችን በሩሲያ እና በባለሥልጣነቷ ላይ እንደሚጥሉ ገልጸዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄምስ ክሌቨርሊ አገራቸው በሩሲያ ላይ ተጨመሪ የንግድ፣ የምጣኔ ሃብት እና የገንዘብ ዝውውር ላይ እርምጃ ትወስዳለች ብለዋል።
አዲሷ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ፣ ፑቲን “የአጠቃላይ አውሮፓን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል አዲስ ኢምፔሪያሊስት፣ የሶቪየትን የሚመስል ፍላጎታቸውን በድጋሚ አሳይተዋል” ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ስብስብ የሆነው የአውሮፓ ምክር ቤት የሩሲያን ግዛቶቹን መጠቅለል ሕጋዊ ተቀባይነት የለውም በማለት እርምጃውን “ያለማወላወል አጥብቀን እናወግዘዋለን” ብለዋል።












