ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን ለመጠቅለል የምታደርገውን ሙከራ አሜሪካ በፍጹም ዕውቅና አትሰጥም - ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን ለመጠቅለል የምታደርገውን ሙከራ አሜሪካ “በፍጹም፣ በፍጹም” ዕውቅና አትሰጥም ሲሉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።
ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት አራት የዩክሬን ግዛቶች ወደ ሩሲያ መቀላቀላቸውን ያውጁበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ንግግራቸው በፊት ነው ባይደን ይህንን የገለጹት።
ሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ዛፖሪዢያ እና ኼርሶን በቅርቡ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ሩሲያ ለመቀላቀል ድምጽ ሰጥተዋል ብሏል ክሬምሊን።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን ሕዝበ ውሳኔውን የይስሙላ ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
አሜሪካም በዚህ ምክንያት በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ ትጥላለች ተብሏል።
“ስለዚህ ጉዳይ በግልፅ መናገር እፈልጋለሁ፣ ሩሲያ በዩክሬን ሉዓላዊ ግዛት ላይ ያቀረበችውን የይገባኛል ጥያቄ አሜሪካ በፍፁም፣ በፍፁም፣ በፍጹም እውቅና አትሰጥም” ብለዋል ባይደን።
ሐሙስ ዕለት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ዛፖሪዢያ እና ኼርሶን ገለልተኛ ግዛቶች ናቸው ሲሉ ዕውቅና የሚሰጡ ሁለት አዋጆችን ፈርማዋል። ይህም ሩሲያን እንዲቀላቀሉ መንገድ ጠርጓል።
በሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተጋሩት ሰነዶች እንደሚያመለክቱት ለሁለቱ ዕውቅና የተሰጠው በዓለም አቀፍ ሕግ እና “በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በተደነገገው” መሠረት ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ግን በኃይል የማንኛውም አገር ግዛት መጠቅለል የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርን እና ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር ነው ብለዋል።
“በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ቦታ የሌለው አደገኛ ድርጊት” ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ከፑቲን ጋር በነበራቸው የስልክ ጥሪም በዕቅዱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ገልጸዋል ።
የሩሲያው መሪ ውጥረቱን እንዲቀንሱ እና ከዩክሬን ጋር ለሚደረግ የሠላም ድርድር ሌላ እድል እንዲሰጡ ጠይቀዋል ሲል ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ቱርክ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመሆን በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተደረገውን ድርድር አሸማግላለች።
በጥቁር ባሕር በኩል ወደ ውጭ የሚላከው የእህል ጭነት እንዲጀመርም ከስምምነት በመድረስ የተሳካ ሥራ ተከናውኗል።
የፑቲንን ዕውቅና ለማከናወን ሐሙስ ዕለት ሞስኮ ውስጥ ዝግጅት ሲካሄድ ነበር። በቀዩ አደባባይ የአራቱን ክልሎች የሩሲያ አካል መሆን በሚገልጹ ቢልቦርዶች ያጌጠ የሙዚቃ ዝግጅት ተሰናድቷል።
ተቀባይነት ያላገኘ ሕዝበ ውሳኔን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ የደቡባዊ ክሪሚያ መሬትን ወደ ግዛቷ ቀላቅላለች።
ምዕራባውያን የሚሉት ምንም ይሁን ምን የሩሲያ ሁለቱ ምክር ቤቶች በሚቀጥለው ሳምንት እርምጃውን በይፋ ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, NATALIA KOLESNIKOVA/AFP
የዩክሬን ግዛቶችን በመቀላቀል የሩሲያ ግዛት በምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው ሲሉ ፑቲን ለመከራከር ተስፋ አድርገዋል።
በዚህም አንዳንድ መንግሥታት ለኪዬቭ የሚያደርጉትን ወታደራዊ እርዳታ ሊያቆሙ እንደሚችሉ ያስባሉ።
ኪዬቭ ግን በጦር ሜዳ ላይ ምንም ነገር እንደማይለወጥ ተናግራለች።
ውህደቱ ባለፈው ሳምንት በአራቱም ክልሎች ለአምስት ቀናት ከተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ በኋላ የመጣ ነው።
ሩሲያ ምርጫው ፍትሃዊ እንደነበር እና ሙሉ በሙሉ ሩሲያን እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ተናግራለች።
ነገር ግን በገለልተኛ ወገን ቁጥጥር ያልተደረገ ከመሆን ባለፈ የታጠቁ የሩሲያ ወታደሮች ሰዎች ድምጽ እንዲሰጡ ያስፈራሩ እንደነበር ሪፖርቶች በሰፊው ተሰራጭተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ “የይስሙላ ሕዝበ ውሳኔዎች” ዋጋ ቢስ ናቸው ብለዋል። አማካሪያቸው ማይካሂሎ ፖዶሊያክ ደግሞ “የጅምላ ብጥብጥ” ብለዋቸዋል።












