በሳዑዲ አረቢያ በሃይማኖት ተጓዦች ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ 20 ሰዎች ሞቱ

አውቶቡስ

የፎቶው ባለመብት, AL EKHBARIYA

ታትሟል

በሳዑዲ አረቢያ የሃይማኖት ተጓዦችን ጭኖ የነበረ አውቶብስ ላይ የትራፊክ አደጋ ደርሶ 20 ሰዎች ሲሞቱ 29 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸው ተዘገበ።

የሳዑዲ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አደጋ የደረሰበት አውቶቡስ የሃይማኖት ተጓዦቹን ወደ የእስልምና እምነት ቅዱስ ከተማ ወደ ሆነችው መካ ይዞ እየሄደ ነበር።

ይሁን እንጂ አውቶቡሱ ሰኞ መጋቢት 18/2015 ዓ.ም. ወደ መዳረሻው እያመራ ሳለ በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ ውስጥ ከድልድይ ጋር ተጋጭቶ ከተገለበጠ በኋላ በእሳት ተያይዟል።

አደጋውን በተመለከተ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አውቶብሱ በእሳት ሲጋይ አሳይተዋል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት የአደጋውን መንስዔ እየመረመርን ነው ይበሉ እንጂ፣ ኦካዘ የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ ተሸከርካሪው የፍሬን ችግር አጋጥሞት ነበር ሲል ዘግቧል።

የሳዑዲ አረቢያው አል አራቢያ የመገናኛ ብዙኃን በበኩሉ በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡት የበርካታ አገራት ዜጎች ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ግን የሳዑዲ ዜጎች ናቸው ብሏል።

የሃይማኖት ተጓዦቹ የኡምራ ተጓዦች እንደነበሩ ተገልጿል። በኡምራ ጉዞ እንደ ሃጂ ጉዞ ሁሉ ተመሳሳይ ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወኑ ቢሆንም ከሃጂ ተጓዦች ጋር ሲነጻጸር የኡምራ ተሳታፊዎች ቁጥር ያነሰ ነው።

ከጥቂት ወራት በኋላ በሃጂ ጉዞ ተሳታፊ የሚሆኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሳዑዲ አረቢያ ይጠበቃሉ።

በሳዑዲ አረቢያ በኡምራ ተጓዦች ላይ የትራፊክ አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

እአአ 2019 ላይ የኡምራ ተጓዦችን አሳፍሮ ከመዲና ወደ መካ ሲጓዝ የነበረ አንድ አውቶቡስ ከሌላ ተሸከርካሪ ጋር ተጋጭቶ የ35 ሰዎች ሕይወት አልፎ ነበር።

በዚህ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡት የአረብ እና የኢሲያ አገራት ዜጎች መሆናቸው ተዘግቦ ነበር።