ቦምብ በማፈንዳት ተጠርጥሮ ለ50 ዓመታት ሲፈለግ የነበረው ጃፓናዊ ሳይገኝ እንዳልቀረ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, NATIONAL POLICE AGENCY
ቦምብ በማፈንዳት ተጠርጥሮ ለ50 ዓመታት ገደማ ሲፈለግ የነበረው ተጠርጣሪ ሳይገኝ እንዳልቀረ ጃፓን አስታወቀች።
ሳቶሺ ኪሪሺማ ይባላል። 49 ዓመታት ሙሉ ‘ይፈለጋል’ የሚል ማስታወቂያ ወጥቶበት ቆይቷል። የፖሊስ ማስታወቂያው ላይ ሳቶሺ ፈገግ ብሎ ይታያል።
በመላው ጃፓን ፖሊስ ጣቢያዎች ይህ ማስታወቂያ ለዓመታት ተለጥፎ ቆይቷል።
ቶኪዮ የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ያለ ግለሰብ ሳቶሺ እኔ ነኝ ብሏል።
በ1970ዎቹ ቦምብ ያፈነዳው ታጣቂ ቡድን አባል እንደነበረና የሚፈለገው ሰው እሱ እንደሆነም ገልጿል።
ፖሊስ የዘረ መል ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ እስከሚመጣ እየጠበቀ ነው።
ግለሰቡ በጸና በካንሰር ታሞ ነው ሆስፒታል የገባው።
ምሥራቅ እስያዊ የሆነውና ፀረ-ጃፓን የሆነው ታጣቂ ቡድን አክራሪ ግራ ዘመም ስብስብ ሲሆን፣ ከ1972 እስከ 1975 ባሉት ዓመታት ብዙ የቦምብ ጥቃቶች በጃፓን መዲና በማድረስ ተጠያቂ ይደረጋል።
በአንደኛው የቦምብ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።
በ1974 በሚስትቡሺ ዋና መሥሪያ ቤት ነበር የደረሰው።
የጃፓን ብሔራዊ ፖሊስ በድረ ገጹ እንዳለው፣ ይህ ግለሰብ “ፈንጂን ለመቆጣጠር” የወጣ ሕግን ጥሷል።
“በተከታታይ ቦምቦች በማፈንዳት በፖሊስ ይፈለጋል” በሚል ነው የተገለጸው።
ግለሰቡ በቤት ውስጥ የተሠራ ቦምብ በመቅበር እንዲሁም እንዲፈነዳ በማድረግ ነበር ሲፈልግ የነበረው።
በዚህ በ1975 በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ በቶኪዮ ጊንዛ ግዛት የሚገኝ ሕንጻ በከፊል ጉዳት ደርሶበታል።
ሲፈለግ የነበረው ይህ ግለሰብ ከ49 ዓመታት በኋላ ነው ሳይገኝ አልቀረም የተባለው። አሁን 70 ዓመት ሆኖታል።
ሆስፒታል ሲገባ የተጠቀመው ሌላ ስም ነበር።
አሁን ግን ወደ ሕይወቱ ፍጻሜ አቅራቢያ እውነተኛ ስሙን ለመግለጽ እንደሚፈልግ ለሆስፒታሉ ሠራተኞች ገልጿል።
ሆስፒታሉ እንዳለው ከዚህ በኋላ በሕይወት የሚቆየው ለጥቂት ወራት ነው።












