በዘውዲቱ ሆስፒታል አንዲት እናት 6 ኪሎግራም የሚመዝን ህጻን ተገላገለች

ስድስት ኪሎግራም የሚመዝነው ህጻን

የፎቶው ባለመብት, Dr. Reta Tizazu

የምስሉ መግለጫ, ስድስት ኪሎግራም የሚመዝነው ህጻን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአዲስ አበባ በሚገኘው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል አንዲት እናት 6 ኪሎግራም ክብደት ያለው ህጻን በቀዶ ህክምና መገለገሏን የሆስፒታሉ የማህጻንና ጽንስ ክፍል ኃላፊ እና ባለሙያ ዶክተር ረታ ትዕዛዙ ለቢቢሲ ገለጹ።

ህጻኑ በአሁኑ ወቅት በጤንነት ላይ ቢሆንም ከመፋፋቱ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመመርመር በጨቅላ ጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ገብቶ ህክምና እየተደረገለት እንደሚገኝም ዶክተሩ አስረድተዋል።

ህጻኑ ከተወለደ በኋላ የግሉኮስ መቆጣጠር ችግር ገጥሞት እንደነበር የሚጠቅሱት ዶክተሩ ከልጁ መፋፋት እና እናቱ ስኳር ታማሚ መሆኗን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከናወኑ ምርመራዎች አሉ ብለዋል።

የስኳር ታማሚ የሆነችው ነፍሰ ጡሯ ወደ ማዕከሉ ከቀናት በፊት ስትመጣ እርግዝናዋ ወደ 38 ሳምንታት ደርሶ ነበር።

እንዲህ አይነት ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት የስኳር ህመሙን ለማከም ጥረት እንደሚያደርጉ የገለጹት ዶክተሩ ይህች በ30ዎቹ ዕድሜ የምትገኘው ነፍሰ ጡር ግን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነበር ይላሉ።

በአልትራሳውንድ ልጁ ሲታይ ትልቅ በመሆኑ በምጥ መውለድ እንደማትችል ተረድተው ቀደም ብላ በቀዶ ህክምና እንድትወልድ ውሳኔ ላይ ተደረሰ ብለዋል ዶክተሩ።

ከትናንት በስቲያ ታህሳስ 16፣ 2017 በተደረገላት ቀዶ ህክምና ስድስት ኪሎግራም የሚመዝን ልጅ ተገላግላለች።

በዓለም ክብደት ያለው ህፃን በመውለድ ክብረወሰን የያዘችው ካርሜሊና ፌዴላ የተባለች እናት ናት። በአውሮፓውያኑ 1955 በጣልያን የተገላገለችው ልጅ 10.2 ኪሎግራም እንደሚመዝን መረጃዎች ያሳያሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ ይሄንን ያህል ኪሎ የሚመዝን ህጻን ስለመወለዱ እስካሁን መረጃም ሆነ ጽሁፍ እንዳላገኙ ጠቅሰው "ትልቁ ሳይሆን" እንደማይቀር ዶክተሩ ተናግረዋል።

በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የፋፋ ልጅ የሚባለው ከ4-4.5 ኪሎ መሆኑን ገልጸዋል።በኢትዮጵያ ደግሞ ካለው የአመጋገብ ችግር ጋር ተያይዞ 4 ኪሎ ትልቁ ነው ይላሉ።

አንዲት እናት 4 ኪሎ ክብደት ጽንስ ካላት ጉዳት ስለሚያስከትል አምጣ እንድትወልድ እንደማይደረግ ዶክተሩ ይናገራሉ።

እንዲህ ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ ፋፍተው የሚወለዱበት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ የሚጠቅሱት ዶክተር ረታ አንደኛው ምክንያት በዘር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እንደ ስኳር ያሉ ተጓዳኝ ህመሞች ናቸው።

"ስኳር የነፍሰ ጡሯን የሜታቦሊዝም [የሰውነት ተግባር] ሁኔታ ስለሚቀይረው ይሄ በልጁ ላይ ተጽእኖ ያመጣ እና የግሉኮሱስ አጠቃቀሙን ስለሚያዛባው እንዲፋፋ ያደርገዋል" ይላሉ። ይህ የተለመደ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ቀድሞ በሚታወቅበት ክትትል እንደሚደረግ የሚጠቅሱት ዶክተሩ "የነፍሰ ጡሯ በደሟ ውስጥ ያለው ግሉኮስ ሲስተካከል የጽንሱም አብሮ እንደሚስተካከከል" ገልጸዋል።

ሌሎች ህመሞች እንደሚኖሩ ጠቅሰው የስኳር ህመም ግን የተለመደው ነው ይላሉ።

ሌላኛው የሰውነት ተግባራትን የሚያስተጓጉሉ የጄኔቲክ (የዘረመልን) ህመሞች በሚኖሩበት ወቅትም እንዲሁ ልጆች ከተለመደው ውጭ ሊፋፉ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ዶክተሩ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ነፍሰጡሮች የህክምና አገልግሎት ወደተሟሉባቸው የጤና ተቋማት በቶሎ እንዲያመሩ በዚህ አጋጣሚ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ስድስት ኪሎግራም የሚመዝነውን ህጻን የወለደችው እናት በጤንነት ላይ እንዳለች ጠቅሰው የስኳር ህመሟም ክትትል እየተደረገላት ነው ብለዋል።