ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኡጋንዳ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅት ላይ በርካታ ሰዎች ተረጋግጠው ሕይወታቸው አለፈ
በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ በአዲስ ዓመት ዋዜማ የርችት ሥነ-ስርዓት ለመመልከት በተሰባሰቡ ሰዎች መካከል በተፈጠረ መረጋገጥ ቢያንስ የ9 ሰዎች ሕይወት አለፈ።
የርችት ሥነ-ስርዓት በተዘጋጀበት የገበያ ማዕከል በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል በርካታ ሕጻናት እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ጓደኛውን በአደጋው ያጣው አንድ የዓይን እማኝ መረጋገጡ የተፈጠረው ሰዎች በተቃራኒ አቅጣጫ መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ ነው ብሏል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተጥለው የነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦች ከተነሱ በኋላ ነበር ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ክብረ በዓል ሲባል ሰዎች እንዲሰባሰቡ የተፈቀደው።
የካምፓላ ፖሊስ እንዳለው ፍሪደም ሲቲ ሞል በተሰኘው የገበያ ማዕከል የሙዚቃ ድግስ በነበረው ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ተገኝቶ ነበር።
የሰዎች መረጋገጥ ያጋጠመው የአዲስ ዓመት የርችት ስነ-ስርዓትን ተመልክተው ለሙዚቃው ድግስ ዳግም ወደ የገበያ ማዕከሉ ለመግባት ሲሞክሩ መሆኑ ተገልጿል።
ሕይወታቸውን ካጡት 9 ሰዎች መካከል 5ቱ ተረጋግጠው የሞቱት “ሕጻናት ወይም ታዳጊዎች” ናቸው ተብሎ ተገልጿል።
ራማዳን አፕሆንጎ የተባለ የዓይን እማኝ ኤንቲቪ ለተባለ የአገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሟቾች መካከል አንዷ ጓደኛው እንደሆነች ተናግሯል።
“እየተዝናናች ነበር፤ ጥሩ ግዜ እያሳለፈች ነበር . . . ነገር ግን በአየር እጥረት ምክንያት ሞተች” ብሏል።
የካምፓላ ፖሊስ ክስተቱን በተመለከተ ምርመራ እያደረኩ ነው ብሏል።