የቻይና ሳይንቲስቶች በአዲስ ቫይረስ የተያዙ 35 ሰዎችን አገኙ

ሽሪው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቫይረሱ መነሻ ይሆናሉ ተብለው የሚታመኑት ሽሪው የተሰኙት አይጥ መሰል እንስሳት ናቸው
ታትሟል

ቻይና ውስጥ ከእንስሳ ወደ ሰው የተላለፈ ነው በተባለ አዲስ ቫይረስ የተያዙ ከ30 በላይ ሰዎች ማግኘታቸውን ሳይንቲስቶች አሳወቁ።

የቻይና ሳይንቲስቶች በርካታ ሰዎች የተያዙበትን ይህንን ከእንስሳ ወደ ሰው የተላለፈ ነው የተባለ አዲስ የቫይረስ አይነትን ለመለየት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውም ተነግሯል።

በምሥራቃዊ የቻይና ሻንዶንግ እና ሔናን ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ 35 ህሙማን ላይ የተገኘው ይህ አዲሱ ቫይረስ ‘ላንግያ ሄኒፓቫይረስ’ ወይም ‘ላይቪ’ እንደሚባል ተገልጿል።

በቫይረሱ በተያዙ በበርካቶቹ ሰዎች ላይ ትኩሳት፣ ድካም እና ሳልን የመሳሰሉ ምልክቶች እንደታዩባቸው ሳይንቲስቶቹ አመልክተዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ምናልባትም ከእንስሳት ጋር በሚደረግ ንክኪ ሳይጋባባቸው እንደማይቀር ተገምቷል።

አስካሁን ይህ ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፍ እንደሆነ የሚያመለክት መረጃ የለም።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ቫይረሱ በዋናነት ‘ሽሪው’ በተባሉ አይጥ መሰል እንስሳት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የዚህ ቫይረስ መገኘት ይፋ የሆነው በቻይና፣ በሲንጋፖር እና በአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ተጽፎ በዚህ ወር ‘በኒው ኢንግላንድ ሜዲካል ጆርናል’ ላይ በታተመ ተብዳቤ ላይ ከተጠቀሰ በኋላ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከተመራማሪዎቹ አንዱ እና ሲንጋፖር ውስጥ በሚገኝ የህክምና ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት ዋንግ ሊፋ የቻይና መንግሥት ንብረት ለሆነው ‘ግሎባል ታይምስ’ እንደተናገሩት እስካሁን ባለው መረጃ አዲሱ ቫይረስ ገዳይ ወይም በጣም ከባድ የሚባል ስላልሆነ “መሸበር አያስፈልግም” ብለዋል።

ነገር ግን ሰዎችን ሲይዙ ሊገመት የማይችል ውጤት የሚኖራቸው የቫይረስ ዝርያዎች በተፈጥሮ አካባቢ ውስጥ ሊኖሩ ስለሚችሉ ንቁ ሆኖ መከታተል አስፈላጊ ነው ሲሉ ዋንግ መክረዋል።

ሳይንቲስቶቹ ምርመራ ካደረጉባቸው ሽሪው ከተባሉት እንስሳት መካከል በ27 በመቶው ላይ ቫይረሱ በመገኘቱ እነዚህ እንስሳት ቫይረሱ በስፋት የሚገኝባቸው ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ምርመራ ከተደረገባቸው እንስሳት መካከል ቫይረሱ 5 በመቶ በውሾች ላይ እና 2 በመቶው በፍየሎች ላይ ተገኝቷል።

ባለፈው እሁድ የታይዋን የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳለው የዚህን ‘ላይቪ’ ቫይረስ ክስተትን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን አስታውቋል።

ይህ ቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰው ከሚተላለፉ ቫይረሶች የሚመደብ ሲሆን፣ እንዲህ አይነቶቹ ቫይረሶች በስፋት የሚገኙ ሲሆን ከፍተኛ ትኩረት መሳብ የጀመሩት ግን የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ነው።

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ሳይንቲስቶች እንደሚገምቱት ከሚታወቁት እና አዲስ በሰው ላይ ከሚከሰቱ በሽታዎች ውስጥ ከአራቱ ሦስቱ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው።

የዱር እንስሳትን ለተለያዩ ግልጋሎት ከማዋል እና ከአየር ፀባይ ለውጥ ጋር ተያያዞ እንዲህ አይነቶቹ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች የበለጠ ሊስፋፉ እንደሚችሉ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ከዚህ ቀደም አስጠንቅቆ ነበር።

አንዳንድ ከእንስሳት የሚተላለፉ ቫይረሶች ለሕይወት በእጅጉ አስጊ የሚሆኑ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ወቅት እየጠበቀ እስያ ውስጥ በሰዎችና በእስሳት ላይ የሚከሰተው ‘ኒፓህ’ እና በመጀመሪያ አውስትራሊያ ውስጥ ፈረሶች ላይ የተገኘው ‘ሄንድራ’ የተባለው ቫይረስ ይጠቀሳሉ።

አሁን ከተገኘው ቫይረስ ጋር የሚዛመድ ሌላ ቫይረስ እነዚሁ ሽሪው በተባሉት እንስሳት እና የሌሊት ወፎች እንዲሁም አይጦች ላይ ተገኝቷል።