ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ አውሮፓ የምትልከውን ጋዝ በመቀነስ “የጋዝ ጦርነት” ከፍታለች ሲሉ ዜሌንስኪ ከሰሱ
ሩሲያ ወደ ጀርመን ጋዝ በምታስተላልፍበት ከባሕር በታች በሚገኘው ቱቦ ኖርድ ስትሪም 1 የምትለቀውን የጋዝ መጠን ቀነሰች።
ይህንንም ተከትሎ ሩሲያ አውሮፓ ላይ “የጋዝ ጦርነት” አውጃለች ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከሰዋል።
የሩሲያው ጋዝ አምራች ጋዝፕሮም እንዳለው ግን፣ ወደ ጀርመን የሚለቀቀው የጋዝ መጠን እንዲቀንስ የተደረገው በጋዝ መተላለፊያው ጥገና እየተካሄደ ስለሆነ ነው።
ዜሌንስኪ ግን ይህ የሩሲያ ምክንያት አልተዋጠላቸውም።
ሩሲያ “የጋዝ ምርት በማፈን የአውሮፓን ሕዝብ ለማሸበር እየሞከረች ነው” ሲሉም ከሰዋል።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል በቅርቡ የተደረሰ ስምምነትን ተከትሎ ከዩክሬን ወደብ የጥራጥሬ ምርቶች ወደተለያዩ አገራት መላክ እንደሚጀምሩ ተስፋ አለ።
የሩሲያው ጋዝፕሮም ወደ ጀርመን የሚላከውን የጋዝ መጠን የቀነስኩት ለጥገና ሥራ ብዬ ነው ቢልም፣ ጀርመን ግን የጋዝ መጠንን መቀነስ እና ጥገና የሚያገናኛቸው ነገር የለም ስትል ተከራክራለች።
ኖርድ ስትሪም 1 የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የሚያልፈው በአትላንቲክ ውቅያኖሱ የባልቲክ ባሕር ሥር ሲሆን፤ ከሩሲያ ወደ ጀርመን ጋዝ ያጓጉዛል።
ላለፉት ሳምንታት የሚላከው የጋዝ መጠን ከዚህ ቀደሙ ያነሰ ነው።
በዚህ ወር መባቻ ለ10 ቀናት ያህል ለጥገና ተብሎ ማስተላለፊያ ቱቦው ተዘግቶ እንደነበርም ይታወሳል።
ሩሲያ ለአውሮፓ ኅብረት 40 በመቶ ጋዝ ታቀርባለች።
ይህንን የጋዝ አቅርቦት ሩሲያ እንደ እጅ አዙር መዋጊያ መሣሪያ እየተጠቀመች ነው ብላ አውሮፓ ትከሳለች።
“አውሮፓን በጋዝ መቅጣት በየወሩ እየተባባሰ መጥቷል። ድርጊቱ የአውሮፓውያንን ሕይወት ለማመሳቀል በአሸባሪ መንግሥት የተፈጸመ ነው” ሲሉ ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
መጪውን የአውሮፓውያን ክረምት ፈታኝ ለማድረግ ታልሞ የተደረገ ነው ሲሉም ከሰዋል።
ይህም በዋነኛነት ድሃ አውሮፓውያንን እንደሚጎዳ ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት አገራት ዋነኛ የጋዝ ምንጫቸው ሩሲያ ናት። የጋዝ መጠን በመቀነሱ ግን አጣብቂኝ ውስጥ እየገቡ ነው። በተለይም መጪው ክረምት ያሰጋቸዋል።
የአውሮፓ የኢነርጂ ሚኒስቴሮች በቅርቡ ተገናኝተው ውይይት በማድረግ አንዳች የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሴላ ቮን ደር ሌይን፣ ሩሲያ ወደ አውሮፓ የምትልከውን ጋዝ ሙሉ በሙሉ የምታቆምበት ዕድል የለም ማለታቸው አይዘነጋም።
ከሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በተቀረው ዓለምም የጋዝ ዋጋ ንረት ተስተውሏል።