ሩሲያ የዩክሬን ጦር ሠራዊት አባላትን በጦር ወንጀል ከሰሰች

ታትሟል

ሞስኮ 92 የዩክሬን ጦር ሠራዊት አባላት ላይ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል በመፈጸም ክስ እንደተመሠረተባቸው የሩሲያ የምርመራ ኮሚቴ ኃላፊ አስታወቁ።

አሌክሳንደር ባስትሪኪን ለመንግሥታዊው የዜና አውታር ሮሲስካያ ጋዜጣ እንደተናገሩት ከ1 ሺህ 300 በላይ የወንጀል ምርመራዎች ተጀምረዋል።

አክለውም ገለልተኛ ያሉት እንደ ቦሊቪያ፣ ኢራን እና ሶሪያ በአባልነት የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ጉዳዩን እንደሚመረምር ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

51 የጦር አዛዦችን ጨምሮ 96 ሰዎች እየተፈለጉ ይገኛሉ ብለዋል።

ዩክሬናዊያኑ "በሰው ልጅ ሠላም እና ደኅንነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች" ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉም ለጋዜጣው ተናግረዋል።

ቢቢሲ በቃለ መጠይቁ ላይ የቀረቡትን ውንጀላዎች ማረጋገጥ ያልቻለ ሲሆን ኪዬቭ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።

ዩክሬንም የበኩሏን ምርመራ እያከናወነች ነው። የሩሲያ ወረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተፈጸሙ የተባሉ ከ21,000 በላይ የጦር ወንጀሎችን እና የጥቃቶችን እየመረመርኩነው ብላለች።

ዩክሬንን "የወንጀል ማዕከል" ሲል የገለጻት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የምርመራ እና የፎረንሲክስ ባለሙያዎችን ቡድን ወደ ስፍራው ልኳል።

ክሬምሊን ሁሉንም የጦር ወንጀሎችንም ሆነ ሲቪሎችን ዒላማ አድርጋለች መባሉን ታስተባብላለች። ዩክሬን መሠረተ ልማቶቿን እንደደበደበች እና ሠላማዊ ዜጎቿን መግደሏን በመግለጽ በተደጋጋሚ ትከሳለች። ውንጀላው በዓለም አቀፍ መሪዎች በበርካታ አጋጣሚዎች ውድቅ አድርገውታል።

ባስትሪኪን ምዕራባውያንን በግልፅ 'የዩክሬን ብሔርተኝነት' ይደግፋሉ ሲሉ የከሰሱ ሲሆን ይህ በተባበሩት መንግሥታት በሚደገፍ የፍርድ ሂደት ማለፉ "እጅግ አጠራጣሪ ነው" ብለዋል።

ዩክሬን በኒዮ ናዚዎች ተወራለች በማለት ሞስኮ ትገልጻለች። ይህንንም “ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” ብላ ለጠራችው እርምጃ ምክንያት እንደሆናት በተደጋጋሚ ተናግራለች።

ባስትሪኪን ከዚህ ይልቅ በተለይም እንደ ሶሪያ፣ ኢራን እና ቦሊቪያ ካሉና "በዩክሬን ጉዳይ ገለልተኛ አቋም" ካላቸው አገራት ጋር ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ሐሳብ አቅርበዋል።

በመቶዎች ከሚቆጠሩ የዩክሬን ወታደራዊ እና ፖለቲከኞች በተጨማሪ ምንም ማስረጃ ሳያቀርቡ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን በማዘጋጀት የከሰሷቸው የዩክሬን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሠራተኞች ላይም ምርመራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ከዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኔዘርላንድስ እና ከጆርጂያ በተወጣጡ ተጠርጣሪ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ዙሪያ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለጋዜጣው ተናግረዋል።