ኢራቃዊቷን በባርነት ያቆየችው ጀርመናዊት የአይ ኤስ አባል እስር ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, AFP
የእስላማዊ መንግሥት ቡድኑን (አይኤስ)ን የተቀላቀለችው ጀርመናዊት፣ ያዚዲ በመባል የሚታወቁት የኢራቅ ማኅበረሰብ አባል የሆነችውን ሴት በባርነት ማቆየትን ጨምሮ በሌሎች ወንጀሎች የዘጠኝ ዓመታት እስር ተፈረደባት።
ጀርመናዊቷ በሰብዓዊነት ላይ በፈፀመችው ወንጀሎች እና የውጭ የሽብርተኛ ድርጅትን በመቀላቀል ጥፋተኛ ሆና ተገኝታለች።
በምዕራብ ኮብሌዝ ከተማ የሚገኘው ፍርድ ቤት እንዳለው የ37 ዓመቷ ወጣት ከባለቤቷ ጋር በሶሪያ እና በኢራቅ እየኖሩ ባሉበት ወቅት ያዚዲ ሴት ላይ ለሦስት ዓመታት ጥቃት ስታደርስባት ነበር።
ከዚህም ባሻገር ባለቤቷ ግለሰቧን እንዲደፍራትና እንዲደበድባት ስታበረታታው እንደነበርም ተመልክቷል።
የፍርድ ሒደቱ በተጀመረበት ጥር ወር ላይ አቃቤ ሕግ “ ይህ ሁሉ የያዚዲ እምነትን ለማጥፋት የሚደረግን የአይ ኤስን ግልጽ ዓላማ የሚያሳይ ነው።” ብሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2014 የአይ ኤስ ተዋጊዎች በሰሜን ኢራቅ የያዚድ እምነት ተከታዮች ቀደምት ሕዝቦች በሚኖሩበት እምብርት ገብተው ጥቃት ፈፅመው ነበር።
በዚህም ምክንያት ያዚዲዎች ወደ ሲንጃር ተራራ ለመሰደድ ተገደዋል። በርካቶችም የተገደሉ ሲሆን 7 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶች ተይዘው ለባርነት ተደርገዋል።
ከእነዚህ መካከል ተከሳሿ ናዲን ኬ እና ባለቤቷ ወደ ኢራቅ ሞሱል ባመሩበት ጊዜ ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ በባርነት የተገለገሉባት ወጣት ሴት እንደምትገኝበት አቃቤ ሕግ አስረድቷል።
ግለሰቦቹ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ወደ ሶሪያ በመሄድ የአይ ኤስ ቡድንን የተቀላቀሉ ሲሆን በኋላ ላይም በወቅቱ በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከነበረችው ወጣት ሴት ጋር አብረው ተመልሰዋል።
ከዚያም መጋቢት 2019 ላይ ናዲን ኬ እና ቤተሰቦቿ ሶሪያ ውስጥ እያሉ በኩርድ ኃይሎች ሊያዙ ችለዋል።
ናዲን ኬ የታሰረችው ባለፈው ዓመት ወደ ጀርመን ከተመለሰች በኋላ ነበር።
በፍርድ ሒደቱ ወቅትም ግለሰቧ ያዚዲ ሴትን ባሪያ አድርጋለች መባሏን የተቃወመች ሲሆን፣ነገር ግን የተሻለ ነገር ልታደርግላት ትችል እንደነበር ተናግራለች።
ተጠቂዋ በ2019 ነጻ የወጣች ሲሆን የካቲት ወር ላይ በተካሄደው ችሎት ላይ ተገኝታ ምስክርነት ሰጥታለች። ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ችሎት ላይም ተገኝታለች።
እንደ አሶሼትድ ፕረስ የዜና ወኪል ከሆነ ተጠቂዋ ተመሳሳይ ወንጀል የፈፀሙ ሁሉ ወደ ሕግ እንደሚቀርቡ ተስፋ እንዳላት ጠበቃዋ ተናግረዋል።
የቀድሞ የአይ ኤስ አባላት የያዚዲ እምነት ተከታዮችን በመግደልና ጥቃት በማድረስ መከሰሳቸውን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጀርመን በርካታ ችሎቶች ተካሂደዋል።
ጥቅምት 2021 ላይ እንዲት ሴት፣ ባለቤቷ እና እርሷ ባሪያ ያደረጓትን ያዚዲ ታዳጊን በመግደል ወንጀል የ10 ዓመት እስር ተፈርዶባታል።
ከአንድ ወር በኋላም የጀርመን ፍርድ ቤት አይ ኤስ በያዚዲ ሕዝቦች ላይ የሚፈፅመው የዘር ማጥፋት እንደሆነ በመቀበል የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጥቷል።












