ሕንድ ውስጥ በመርዘኛ ጋዝ ምክንያት ቢያንስ 11 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜናዊ ሕንድ ውስጥ ባፈተለከ መርዘኛ ጋዝ ምክንያት ቢያንስ የ11 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተዘገበ።
በሕንድ ፑንጃብ ግዛት ውስጥ ባለችው የወደብ ከተማዋ ሉድሃይና ውስጥ በደረሰው በዚህ አደጋ ከሞቱት ሰዎች ውስጥ ሴቶች እና ሕጻንት ይገኙበታል።
በመርዘኛ ጋዙ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪም በርካታ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ እራሳቸውን ስተው ተገኝተዋል። አራት ሰዎች በሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው ነው።
ብዙ ሰዎች የመተንፈስ ችግር እንዳጋጠማቸው ከተነገረ በኋላ አደጋው የደረሰበት አካባቢ እንዲዘጋ እና ነዋሪዎች እንዲወጡ ተደርጓል።
የመርዘኛ ጋዙ ምንጭ ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ አንድ ባለሥልጣን ግን ከመሬት በታች ካለ ቱቦ ውስጥ አፈትልኮ የወጣ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የሉድሃይን ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ ሱራብሂ ማሊክን ፕሬስ ትረስት ኢንዲያ ለተባለው ዜና ወኪል እንደተናገሩት “በከተማዋ ውስጥ ካሉ ጉድጓዶች ናሙናዎችን ወስደን እንመረምራለን። በጉድጓዶች ውስጥ ሜቱን የተባለው ኬሚካል ሊፈጠር ይችላል” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አደጋው ያጋጠመው ከአንድ የወተት መሸጫ መደብር አቅራቢያ መሆኑን ራጂንዳር ፓል ኩር ቺና የተባሉ የከተማዋ የምክር ቤት አባል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
“በጠዋት ወተት ከመደብሩ ለመግዛት የመጡ ሰዎች ውጪ ላይ እራሳቸውን ስተው ወድቀው ነበር” ብለዋል።
የሕንድ ብሔራዊ የአደጋ ምላሽ ግብረ ኃይል ቡድን ምርመራ እንዲያደረግ ወደ ስፍራው ተልኳል ተብሏል።
አደጋው የደረሰበት የፑንጃብ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ሉድሃይን ውስጥ ጊያስፑራ በተባለ ስፍራ ሲሆን፣ በአቅራቢያው በርካታ ፋብሪካዎች ይገኛሉ።
ከኢንዱስትሪ አካባቢዎች አፈትልከው የሚወጡ የአደገኛ ጋዞች ክስተት በሕንድ ውስጥ ብዙም ያልተለመደ ነገር አይደለም።
ከሦስት ኣመት በፊት በአንድራ ፕራዴሽ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቪሳኻፓትናም በተባለችው ከተማ ከነበረ የኬሚካል ፋብሪካ ባፈተለከ ጋዝ ምክንያት ቢያንስ 12 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
በአውሮፓውያኑ 1984 ደግሞ ቦፓል በምትባለው ከተማ ውስጥ ካለ የፀረ ተባይ ማምረጃ ፋብሪካ ባፈተለከ ኬሚካል ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለሞት ተዳርገዋል። ይህም በዓለም አስከፊው የኢንዱስትሪ አደጋ ተብሎ ተመዝግቧል።












