ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ የሚደረገው የስደተኞች ጉዞ ጉዳይ ይግባኝ ሊጠየቅበት ነው

ታትሟል

የዩኬ መንግሥት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ማጋዝ መጀመሩን የተቃወሙ ሰዎች ጉዳዩን ሰኞ ዕለት ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይግባኝ ሊጠይቁ ነው።

ከፍተኛው ፍርድ ቤት የመጀመሪያው ዙር ስደተኞችን የማጓጓዝ ሥራ እንዲካሄድ ፈቃድ መስጠቱ ተሰምቷል።

31 ሰዎች ማክሰኞ ዕለት በአውሮፕላን ተጭነው ወደ ሩዋንዳ እንደሚወሰዱ ተነግሯቸዋል።

በዚህ ዓመት ተጨማሪ አውሮፕላኖች ስደተኞችን ጭነው ወደ ሩዋንዳ ይሄዳሉ።

የዌልሱ ልዑል ቻርልስ በዚህ የመንግሥት ዕቅድ ደስተኛ እንዳልሆኑ የዩኬ ጋዜጦች አስነብበዋል።

ልዑሉ በያዝነው ወር ወደ ምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሃገር ንግሥቷን ወክለው እንደሚያቀኑ ታውቋል።

የልዑሉ ጉዞ ዓላማ ኪጋሊ ውስጥ የኮመንዌልዝ ሃገራት መሪዎች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ነው።

የልዑሉ ተወካይ እንደሚሉት ልዑሉ "ፖለቲካዊ አስተያየቶችን" ከመስጠት ይቆጠባሉ።

አዲሱ የመንግሥት ፖሊሲ እንደሚለው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የገቡ ሰዎች ወደ ሩዋንዳ ተወስደው እንደ አዲስ ጥገኝነት ይጠይቃሉ።

የቦሪስ ጆንሰን መንግሥት ይህን የሚያደርገው ስደተኞች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የሚያደርጉትን ጉዞ ለመግታት ነው።

በዚህ ዓመት ብቻ ኢንግሊሽ ቻናል የተሰኘውን የባሕር መንገድ ተጠቅመው 10 ሺህ ሰዎች ድንበር አቋርጠዋል።

ነገር ግን ይህን ጉዞ የሚቃወሙ ተሟጋቾች እንደሚሉት ስደተኞች "በግዴታ ከሃገር እንዲወጡ" እየተደረጉ ነው።

ተሟጋቾቹ የመጀመሪያው በረራ እንዳይነሳ ለማድረግና ሰዎች እንዳይሳፈሩ ለማገድ አቅደው ነበር።

ከተሟጋቾቹ መካከል አንዱ ጀስቲስ ስቂፍት አርብ ዕለት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓቴል ዕቅዳቸው እንዲሳካ ሊፈቀድ አይገባውም ብለዋል።

ጀስቲስ አክለው ስደተኞቹ ወደ ሩዋንዳ ከተወሰዱ በኋላ ምቹ ያልሆነ ሁኔታ እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ከጥገኝነት ጠያቂዎቹ መካከል አንዱ የቀድሞ የኢራን ፖሊስ አዛዥ ሩዋንዳ ከሄድኩ በኋላ የኢራን ሰላዮች ሊገሉኝ ይችላሉ የሚል ፍራቻ አለው።

ሰውዬው ኢራን ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ሲነሳ ሰልፈኞች ላይ አልተኩስም በማለቱ ተከሶ ፍርዱን እየተጠባበቀ ሳለ አምልጦ ወደ ቱርክ እንደገባ ከዚያም ጉዳዩን ለዩኬ መንግሥት አሳውቆ ጥገኝነት እንደጠየቀ ይናገራል።

"ሩዋንዳ ሄጄ በሰቀቀን መኖር አልፈልግም። አንደኛዬን ኢራን ተመልሼ የሆነው ቢሆን ይሻለኛል" ሲል አዲሱ ፖሊሲ የፈጠረበትን ስሜት ይገልጣል።

ግለሰቡ ማክሰኞ ዕለት ወደ ሩዋንዳ እንዲሄዱ ስማቸው ከተጠራ ሰዎች መካከል ነው።

የዩኬ መንግሥት ፖሊሲ እንደሚለው ስደተኞቹ ወደ ሩዋንዳ ካቀኑ በኋላ የሚያርፉበት ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል።

ሩዋንዳ ሆነው ጥገኝነት እንደ አዲስ ጠይቀው ወደሚቀበላቸው ሃገር ማቅናት ይችላሉ።

ጥገኝነት ጠይቀው ያልተሳካላቸው ሰዎች ወደ መጡበት ሃገር በግዴታ ሊመለሱ እንደሚችሉ አዲስ ፖሊሲ ያትታል።

እስካሁን 130 ሰዎች ወደ ሩዋንዳ እንደሚያቀኑ ተነግሯቸዋል።