ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ለአውሮፕላን ተጓዦች የኮቪድ-19 ምርመራ ግዴታን አስቀረች
አሜሪካ በአውሮፕላን ከውጭ አገራት የሚገቡ ተጓዦች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመግባታቸው በፊት ሲጠየቅ የነበው የኮቪድ-19 ምርመራ ማረጋገጫ እንዲቀር አደረገች።
ባለሥልጣናቱ አገሪቱ ቫይረሱን ለመዋጋት ባደረገችው “ከፍተኛ መሻሻል” ምክንያት ከቫይረሱ ነጻ የመሆን የምርመራ ውጤት ማቅረብ አስፈላጊነት እንዲያበቃ ማድረጓን አሳውቀዋል።
ይህ ቅድመ ሁኔታ እንዲቀር የጉዞ አገልግሎት ዘርፉ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። በፖሊሲው ምክንያት ብዙዎች መጓዝ ስለሚፈሩ እንግልት ተፈጥሯል ብለዋል።
ለውጡ ከነገ እሁድ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ፖሊሲውን በ90 ቀናት ውስጥ እንደገና ይገመግመዋል። አስተዳደሩ አዳዲስ ዝርያዎች ስጋት ከፈጠሩ ግን ደንቡን ወደነበረበት ከመመለስ “ወደኋላ እንደማይል” ገልጿል።
"ይህን እርምጃ መውሰድ የቻልነው ቫይረሱን በመዋጋት ባደረግነው ከፍተኛ መሻሻል ነው። ህይወት አድን የሆኑ ክትባቶች እና ህክምናዎችን በስፋት እንዲሰራጭ አድርገናል። እነዚህ መፍትሔዎች ከባድ ህመም እና ሞትን ለመከላከል እያገለገሉ ናቸው። በበሽታው ላይም ውጤታማ ሆነዋል። በዩናይትድ ስቴትስ እና በዓለም ዙሪያ በስፋት እየተሰራጩ ያሉ ዝርያዎች አሉ" ሲሉ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
አሜሪካስ ተጓዦች ከበረራ በፊት ባሉት በሦስት ቀናት ውስጥ ምርመራ እንዲያደርጉ ወይም ከቫይረሱ በቅርብ ጊዜ ማገገማቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ አንዲይዙ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ያስተዋወቀችው።
የኦሚክሮን ስርጭት ማየሉን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ባይደን ይህን ፖሊሲ ከበረራ አንድ ቀን በፊት እንዲሆን አድርገው ነበር።
አብዛኞቹ አሜሪካዊ ያልሆኑ ዜጎች ለመጓዝ አሁንም መከተብ ይጠበቅባቸዋል።
ከጥር ወር ጀምሮ በአሜሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። በቅርብ ቀናት ግን ቁጥሩ እያሻቀበ ይገኛል። በክትባት መርሃ ግብሩ ተጽእኖ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከወረርሽኙ ከፍ ካለበት በጣም ያነሰ ሆኗል።
ወረርሽኙ እየቀነሰ በመምጣቱ የጉዞ ፍላጎት መጨመሩን ያየው የጉዞ ዘርፉ፣ አሜሪካ የኮቪድ ምርመራ ግዴታ ፖሊሲዎችን እንደገና ከመገምገም አንጻር ከሌሎች አገራት አንጻር ወደኋላ ቀርታለች ብሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም ልክ እንደ ካናዳ በመጋቢት ሁሉንም የኮቪድ-19 ምርመራ መስፈርቶችን አስወግዳለች። ጣሊያን በዚህ ወር የምርመራ መስፈርቶቿን አንስታለች።
የዩናይትድ ስቴትስ የጉዞ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሮጀር ዶው የፖሊሲው ለውጥ "የአሜሪካን የጉዞ ኢንዱስትሪ ማገገምን ያፋጥናል" ብለዋል። ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ደግሞ "ውጤታማ ያልሆነው” እርምጃ መቋረጡ "በጣም ጥሩ ዜና" ነው ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ ገደቦችን ቀስ በቀስ እያቃለለች ነው።
በሚያዝያ ወር ላይ ፍርድ ቤት የሲዲሲን ትዕዛዝ ውድቅ ካደረገ በኋላ የአሜሪካ ተጓዦች በአውሮፕላኖች ላይ ጭምብል እንዲለብሱ ያስቀመጠችውን መስፈርት አስቀርታለች።
የአሜሪካ የጉዞ ማኅበር ባደረገው ጥናት መሰረት የምርመራው መስፈርት መቅረት በዚህ ዓመት ተጨማሪ 5.4 ሚሊዮን ጎብኚዎችን ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ ያስችላል። ይህም የጉዞ ወጪን በ12 በመቶ ይጨምራል።