ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፓኪስታን መስጊድ ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 47 ሰዎች ሲገደሉ ከ150 በላይ ቆሰሉ
በፓኪስታን ፔሻዋር ከተማ በሚገኝ አንድ መስጊድ ውስጥ በተፈጸመ የከባድ ፍንዳታጥቃት ቢያንስ 47 ሰዎች ተገደሉ።
ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው በመስጊዱ ለጸሎት ተሰብስበው የነበሩ በርካታ የፖሊስ አባላትን ሲሆን፣ ከ150 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በፍንዳታው የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የመስጊዱ አንደኛው ክፍል በፍንዳታው በመውደሙ ሰዎች በፍርስራሽ ውስጥ መቀበራቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የፍንዳታው መንስዔ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
ይሁን እንጂ አንድ ባለሥልጣን፣ ፖሊስ የጥቃቱ ኢላማ እንደነበር እና ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ የፖሊስ ኃይል አባላት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደኅንነት ባለሥልጣናት በበኩላቸው በመስጊዱ ውስጥ በፊት ረድፍ ላይ ተቀምጦ የነበረ አጥፍቶ ጠፊ ራሱ ላይ ማፈንዳቱን ገልጸዋል።
እስካሁን ለደረሰው ፍንዳታ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን ግን የለም።
የፔሻዋር ከተማ ፖሊስ መኮንን ሙሐመድ ኢጃዝ ካን፣ ለፓኪስታን መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት በፍንዳታው ወቅት ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ የፖሊስ መኮንኖች በአካባቢው ነበሩ።
ጥቃቱን ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ በሰጡት መግለጫ ድርጊቱን አውግዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው “ከድርጊቱ ጀርባ ያሉ አካላት ከእስልምና ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። መላው ሕዝብም ሽብርተኝነትን ለመከላከል በአንድነት ቆሟል” ብለዋል።
ፍንዳታው የደረሰው በአፍጋኒስታን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ሰሜን ምዕራቧ ከተማ ከቀትር በኋላ ባለው [ዝሁር] ሶላት ወቅት ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረ እና በቢቢሲ የተረጋገጠ ቪዲዮ እንደሚያሳየው የመስጊዱ ግማሽ ግድግዳ የፈረሰ ሲሆን፣ መስጊዱም በፍርስራሽ ተሞልቷል። ሰዎችም በፍርስራሹ ላይ እየተንጠላጠሉ ለመውጣት ሲሞክሩ ታይተዋል።
በመስጊዱ ውስጥ የነፍስ ማዳን ርብርቡ ቀጥሏል።
ተጨማሪ አስክሬኖች እየወጡ መሆናቸውንም የፔሻዋር ከተማ ምክትል ኮሚሽነር ሻፊኡላህ ካን ተናግረዋል።
“አሁን ላይ ቅድሚያ የምንሰጠው በፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን መታደግ ነው” ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።
የሌዲ ሪዲንግ ሆስፒታል ቃል አቀባይ መሐመድ አሲም፣ በአደጋው ከተጎዱት ሰዎች መካከል የተወሰኑት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በፔሽዋር የሚገኘው ሌዲ ሪዲንግ ሆስፒታል አስቸኳይ ጊዜ አውጇል። እስካሁንም ድረስ በፍንዳታው የተጎዱ ሰዎችን እየተቀበለ መሆኑን ለቢቢሲ የገለጸ ሲሆን የደም ልገሳ ጥሪም አቅርቧል።
በፓኪስታን ዋና መዲና ኢስላማባድ፣ ፖሊስ ከፍተኛ የደኅንነት ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን በከተማዋ መግቢያ እና መውጫ በሮች ያለው ቁጥጥር ጠብቋል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ፔሻዋር ከተማ የቦምብ ፍንዳታ ኢላማ ሆና ነበር። በሺአ መስጊድ ላይ በደረሰው በዚህ አደጋም በርካታ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።