ለስልጣን ሽሚያ የሚደረገው ግጭት በቀጠለባት ሱዳን 56 ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ

sudan

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በሱዳን ለስልጣን ሽሚያ በአገሪቱ ጦር እና በልዩ ኃይል ሚሊሻ አባላት መካከል የሚደረገው ግጭት ቀጥሎ ቢያንስ 56 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

የሱዳን ጦር ኃይል እና ራፒድ ሰፖርት ፎርስ ተብሎ የሚጠራው ፈጥኖ ደራሽ ልዩ የሚሊሻ ኃይል በሱዳን መዲና ካርቱም ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት፣ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎችን ለመቆጣጠር ውጊያ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ቅዳሜ ለሊት ለእሁድ አጥቢያ በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ቀጥሎ ስለመካሄዱ ነዋሪዎች እየገለጹ ነው።

በመዲናዋ ካርቱም 17 ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 25 ሰዎች መገደላቸውን አንድ የዶክተሮች ስብስብ ቡድን ገልጿል። በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ ቢያንስ 595 ሰዎች ተጉድተዋል ብሏል ይህ ኮሚቴ።

ትናንት በሱዳን ከተገደሉት መካከል ሦስት የዓለም ምግብ ድርጅት ሠራተኞች መሆናቸው ተገልጿል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይል፣ ወደ አገሪቱ ጦር ስለሚቀላቀልበት ሁኔታ አንዲሁም ኃይሉን ማን ይመረዋል በሚለው ጉዳይ አለመግባባት ተፈጥሮ ባለፉት ቀናት ውጥረት ሰፍኖ ነበር።

ከካርቱም በተጨማሪ ኦማዱርማን፣ ባህሪ እና ፖርት ሱዳን ግጭት እንዳላ የዓይን እማኖች ገልጸዋል።

ትናንት ቅዳሜ ግጭቱ ከጀመረ በኋላ እርስ በርስ የሚጣረሱ መግለጫዎች ከተዋጊዎቹ በኩል ሲወጡ ነበር።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በካርቱም የሚገኘውን አየር ማረፊያ፣ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ጦር ማዘዣ ስፍራዎች እንዲሁም ቁልፍ ድልድዮችን ተቆጣጥሪያለሁ ይላል።

ጦሩ በበኩሉ የጦር ጀቶችን በመጠቀም የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሎች ጦር ሰፈርን መምታቱን ገልጾ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን ተቆጣጥሬ እገኛለሁ ብሏል።

በሱዳን እየተዋጉ ያሉት እነማን ናቸው?

የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ የሆኑት ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ የሆኑት ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአብደላ ሃምዶክ ሲቪል አስተዳደር በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ አገሪቱ ከእአአ 2021 ጀምሮ በሉዓላዊ ምክር ቤት አማካይነት በጦር ጀነራሎች ስትመራ ቆይታለች።

የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ዋነኛ ሰው ሲሆኑ የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ የሆኑት ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ደግሞ ምክትል ናቸው።

በሱዳን ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር በሁለቱ የጦር አመራሮች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ቆይቷል።

ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር ሲሸጋገር የልዩ ኃይል አባላቱ ወደ አገሪቱ ጦር መቀላቀል አለባቸው በሚለው ከስምምነት ቢደረስም ሁለቱ የጦር ጀነራሎች መቼ በሚለው ሊግባቡ አልቻሉም።

ጀነራል አል-ቡርሃን የሚሊሻ አባላቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ አገሪቱ ጦር መግባት አለባቸው ሲሉ ሄምቲ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ግን የሚመሩት ኃይል ጦሩን የሚቀላቀለው ከ10 ዓመት በኋላ ነው ይላሉ።

ታዲያ ለቀናት ውጥረት ነግሶ ከቆየ በኋላ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ትናንት ግጭት ተቀስቅሷል።

ጀነራል አል-ቡርሃን በአገሪቱ ጦር ላይ ክህደት ተፈጽሟል ሲሉ ሄምቲ ደግሞ ሕግ እያስከበርን ነው ይላሉ።

100 ሺህ አባላት ያሉትን ኃይል የሚመሩት ሄምቲ በሱዳን እጅግ ጠንካራ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ግለሰብ ናቸው። ሄምቲ የሚመሩት የሚሊሻ ቡድን በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወነጀል ሲሆን እአአ 2003 በጀመረው የዳርፉር ግጭት አማጺዎችን ተዋግቷል።

ከዳርፉር በተጨማሪ የሄምቲ ጦር በሊቢያ እንዲሁም ከሳዑዲ መራሹ ኃይል ጎን በመሰለፈ በየመን ተዋግቷል።

የፈጥኖ ደራሽ ሚሊሻ አባላቱ ሜሮዌ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የግብጽ ወታደሮች እጃቸውን ሰጥተዋል ብለው በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ማስረጃ አቅርበዋል።

የግብጽ ጦር ግን የጦር አባላቱ ሱዳን የተገኙት ከሱዳን ወታደሮች ጋር ያጋራ ልምምድ ለማድረግ መሆኑን ገልጾ የጦር አባላቱ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገርኩ ነው ብሏል።

ድንጋጤ እና ፍርሃት

የካርቱም ነዋሪዎቹ ግጭቱ ይከሰታል ብለው እንዳልጠበቁ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ድንገት የተቀስቀሰው ግጭት ተማሪዎችን ጨምሮ ከቤታቸው ርቀው ያሉ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ሰላማዊ ሰዎች እራሳቸውን ለመሸሸግ በዋና ጎዳናዎች ላይ ሲሯሯጡ ታይተዋል።

በመዲናዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ብረት ለበስ እና ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ታይተዋል። በካርቱም አየር ማረፊያም በተኩስ ልውውጥ ምክንያት የመንገደኞች አውሮፕላን በእሳት ተያይዟል።

የሳዑዲ አረቢያው ሳዑዲ ኤየር ኤርባስ አውሮፕላኑ በእሳት መያያዙን ገልጿል። የሳዑዲ እና የግብጽ አየር መንገዶች ወደ ካርቱም የምናደርገውን በረራ ለግዜው አቁመናል ያሉ ሲሆን ጎረቤት አገር ቻድ ደግሞ ከሱዳን የሚያዋስናትን ድንበሯን ዘግታለች።

ካርቱም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ግጭት የማቆም ጥሪ

ግጭቱ ከቀሰቀሰ በኋላ ምዕራባውያን አገራት ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ግጭቱ በአስቸኳይ መቆም አለበት ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ደግሞ ጀነራል አል-ቡርሃን እና ጀነራል ዳጋሎን በስልክ ማነጋገራቸው ተገልጿል።

በካርቱም ያለው የሩሲያ ኤምባሲም በአገሪቱ ያለው ሁኔታ አሳስቦኛል ካለ በኋላ ሁለቱ ኃይሎች በአስቸኳይ ተኩስ ማቆም አላባቸው ብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድም ኃይሎቹ ግጭት አቁመው ወደ ንግግር እንዲመለሱ ጠይቀዋል።