‘የፍልስጤማውያንን ሕጻናት ግድያን የደገፉት’ የኦባማ የቀድሞ ረዳት በቁጥጥር ስር ዋሉ

ስቱዋርት ሼልድዊዝ

የፎቶው ባለመብት, x

ታትሟል

በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን የውጭ ጉዳይ ረዳት የነበሩት ባለሥልጣን በጋዛ የደረሰውን የፍልስጤማውያንን ግድያ በመደገፍ እና የእስልምና እምነትን በማንቋሸሻቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ፖለቲከኛው ኒው ዮርክ ውስጥ አንድ የምግብ ነጋዴ ላይ ነው በሺዎች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ሕጻናት በቂ አይደለም በማለት እንዲሁም ሌሎች ስድቦችን የሰነዘሩት።

ስቱዋርት ሼልድዊዝ የተባሉት የቀድሞው የአሜሪካ ባለሥልጣን በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ በሆነ አንድ ቪዲዮ ላይ ነጋዴውን “አሸባሪ” ሲሉ ይታያሉ። ከክስተቱ በኋላ በሰጡት ቃለ መጠይቅ በቪዲዮ ላይ የሚታዩት ሰው እሳቸው እንደሆኑ አምነዋል።

ሰውዬው ይህንን ያሉበትን ምክንያትንም ሲያስረዱ ነጋዴው ሐማስን የሚደግፍ ቃላት በመጠቅም ለጸብ ጋብዦኛል ብለዋል።

ሞሐመድ ሁሴን ‘ሃላል’ ምግቦችን በኒውዮርክ ከተማ ጎዳናዎች ላይ የሚሸጥ ሲሆን፣ ሐማስን የሚደግፍ አስተያየት አልሰጠሁም ብሏል።

የኒው ዮርክ ፖሊስ ቃለ አቀባይ ከዚህ ክስተት በኋላ የቀድሞው ባለሥልጣን ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን አረጋግጦ፣ የክሱ ዝርዝር ግን ዝግጁ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከባለሥልጣኑ ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ የሆኑ ቪዲዮዎች ከአንድ በላይ ሲሆኑ፣ በቀን ውስጥ በተለያየ ጊዜያት የተቀረጸ መሆኑ ተነግሯል።

በአንደኛው ቪዲዮ ላይ ግለሰቡ “ታውቃለህ? 4 ሺህ የፍልስጤም ሕጸናት ገድለን ከሆነ ያ በቂ አይደለም” ሲሉ ይደመጣሉ።

የኤክስ ወይም በቀድሞ ስሙ ትዊተር መረጃ እንደሚያሳየው 40 ሚሊዮን ጊዜ በታየ ሌላ ቪዲዮ ደግሞ ነጋዴውን ከመዝለፍ አልፈው እጅግ ጸብ ጫሪ ንግግሮችን በነብዩ መሐመድ እና በቁርአን ላይ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ነገሩን ሲታዘብ የነበረ ሌላ ሰው “ሰውዬው ላይ በደል እያደረስክ ነው” ሲል ተሰምቷል።

ይህንን ዘለፋ የፈጸሙት ስቱዋርት ሼልድዊዝ የእስራኤል እና የፍልስጤም ጉዳይን የሚከታተለውን ጽህፈት ቤትን ጨምሮ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ አገልግሎት አላቸው። ።

በተጨማሪም የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ምክር ቤት ዳይሬክተር ሆነው በኦባማ አስተዳደር ወቅት ሠርተዋል።

ስውዬው ዘ ዴይሊ ቢስት ለተባለ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት በቨዲዮው ላይ የሚታዩት እሳቸው መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

“አሸባሪነትን እና የንጹሃን ግድያን የሚቀበል ሰው ለሚሰጠው አስተያየት ምላሽ ያስፈልጋል” ማለታቸውም ተነግሯል።

በሌላ ሚዲያ ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ደግሞ “ይህ ነገር በመፈጠሩ ተጸጽቻለሁ። አዝናለሁ። ነገር ግን ነገሩ በጣም በተካረረበት ሰዓት ማለት የሌለብኝን ነገር ብዬ ሊሆን ይችላል” ማለታቸው ተዘግቧል።

ከዚህ ክስተት በኋላ በርካቶች የቀድሞ ባለሥልጣን ስድብ፣ ዘለፋ እና ማስፈራሪያ ሰለባ ለሆነው ነጋዴ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የኒው ዮርክ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ በኤክስ ገጻቸው “ሙስሊም ጠልነት ጥላቻ ነው። ይህ አይነቱ ክብረነክ ሁኔታ በከተማችን ቦታ የለውም። እናወግዘዋለን። በዚህ ሁኔታ ብቻችንን እንዳልሆንን ስናይ ደግሞ እንደሰታለን” ብለዋል።

ነጋዴው ሁሴን የትውልደ አገሩ ግብፅ ሲሆን ለኒው ዮርክ ፖስት በሰጠው አስተያት ዘለፋ እና ማስፈራሪያ በሰነዘሩበት የቀድሞው ባለሥልጣን ላይ ክስ የመመሥረት ሃሳብ እንዳለው ተናግሯል።