እንግሊዝ በቤሊንግሃም እና ሃሪ ኬን ግቦች ሜክሲኮን አሸንፋ ወደ ሩብ ፍጻሜ አለፈች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እንግሊዝ በአዝቴካ ስታዲየም በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ምርጥ ብቃት አሳይታ ሜክሲኮን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ አለፈች።

እንግሊዝ በቀጣይ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ብራዚልን ያሸነፈችውን ኖርዌይን ትገጥማለች።

በትዕይንት የተሞላው የእንግሊዝ እና ሜክሲኮ ጨዋታ በከባድ የሙቀት ማዕበል ምክንያት ለአንድ ሰዓት ያህል ዘግይቶ ነበር የጀመረው።

እንግሊዞች ጨዋታውን ያሸነፉት ጃሬል ኳንሳህ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ በቀይ ካርድ በመሰናበቱ የጎደለውን ቡድን ይዘው ነው።

ሜክሲኮ እስከዛሬ በዋና ከተማዋ ውስጥ በሚገኘው አዝቴካ ስታዲየም ካደረገቻቸው 89 ጨዋታዎች ውስጥ የተሸነፈችው ሁለቱን ብቻ ነው። እንግሊዞች ወደ ሜዳ ይዘውት የገቡት የተረጋጋ አጨዋወት ግን የበላይነት እንዲይዙ አስችሏቸዋል።

በጨዋታው ድንቅ ብቃት ያሳየው ጁድ ቤሊንግሃም ከእረፍት በፊት በ98 ሰከንዶች ልዩነት ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።

የእንግሊዙ ግብ ጠባቂ ጆርዳን ፒክፎርድም ከሜክሲኳዊው ራውል ጂሜኔዝ የተሰነዘሩትን ሙከራዎች በማዳን ምርጥ ብቃቱን አሳይቷል።

ጁሊያን ኩዊኖኔስ ከእረፍት ሦስት ደቂቃዎች በፊት በጠንካራ አጨራረስ ያስቆጠራትን ግብ ግን ሊያድን አልተቻለውም።

የሜክሲኮ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ያካሄደው በከፍተኛ የደጋፊዎች ጩኸት ታጅቦ ነበር። የእንግሊዙ ኳንሳህ በሜክሲኮው ሄሱስ ጋላርዶ ላይ ጥፋት ሰርቶ ቀይ ካርድ ሲሰጠው የደጋፊዎቹ ጩኸት ጎልቶ ተሰምቷል።

ይሁን እንጂ የሜክሲኮው ግብ ጠባቂ ራውል ራንጌል የግብ ሳጥን ውስጥ የእንግሊዙን አንቶኒ ጎርዶን በመጥለፉ ፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቷል።

ሃሪ ኬን ይህን ፍጹም ቅጣት ምት በማስቆጠር እንግሊዝ በሦስት ግብ እንድትመራ አድርጓል።

ከደቂቃዎች በኋላ ግን ሦስተኛውን ግብ ያስቆጠረው ኬን የግብ ሳጥን ውስጥ ብራየን ጉቴሬዝ ላይ ጥፋት በመፈጸሙ ሜክሲኮ ፍጹም ቅጣት ምት አግኝታለች። ሜክሲኮ ሁለተኛውን ግብ ያስቆጠረችው በዚህ ሰዓት ነው።

በዚህ ግጥሚያ የእንግሊዝ ስመ ጥር ተጫዋቾች ብቃታቸውን አሳይተዋል።

በተለይ ከእረፍት በፊት ሁለት ግብ ያስቆጠረው ቤሊንግሃም፤ ድንቅ ግላዊ ብቃቱን አስመስክሯል።

በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የሜክሲኮው ተከላካይ ሴሳር ሞንቴስ ሊያስቆጥር የነበረውን ግብ በማክሸፍ ቡድኑ መሪነቱን እንደያዘ እረፍት እንዲወጣ ማድረግ ችሏል።

የሜክሲኮው ስታዲየው በሚገኝበት ሥፍራ የተነሳ በከባድ አየር ሁኔታ ውስጥ የተጫወቱት እንግሊዞች፤ አሰላለፋቸውን ቀይረው አምስት ተከላካይ አሰልፈዋል።

በዚህም አሰልጣኙ ቶማስ ቱቼል የሚመራው የእንግሊዝ ቡድን የ11 ደቂቃ ጭማሪ ሰዓትን አልፎ አሸናፊነቱን አስጠብቋል።