የልጅነት ቁስሉን ሌሎችን በመርዳት ለመሻር እየጣረ ያለው ኢትዮጵያዊው መምህር

የፎቶው ባለመብት, Debelo Itana
በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ከተማ አንዲት እናት ለ18 ዓመታት ጎዳና ላይ ኖረዋል።
በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ታሪካቸው ከሰው አፍ ላይ አይጥፋ እንጂ ይህ ነው የሚባል ድጋፍ ያደረገላቸው አልነበረም።
18 ዓመት ጎዳና ላይ ሲያሳልፉ የአእምሮ ጤና እክል ተጨምሮበት በእጃቸው የነበረችውን አንድ ልጅ ዘመድ ሊያሳድግ ወስዶባቸዋል።
“እኚህ እናት መጀመርያ ባለቤታቸው ነበር የሞተባቸው። ቀጥሎ ሁለት ልጆቻቸው ሞቱ። በመጨረሻም ከአንድ ዓመት ሕጻን ልጃቸው ጋር ብቻቸውን ቀርተው ነበር” ይላል መምህር ደበሎ።
መምህር ደበሎ ኢታና ተወልዶ ያደገው በምዕራብ ወለጋ ዞን በቂልጡ ካራ ወረዳ ውስጥ ነው።
በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ጤና ኮሌጅ ውስጥ መምህር ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በወለጋ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪውን በመማር ላይ ይገኛል።
እኚህ እናት ከባለቤታቸው እና ሁለት ልጆቻቸው ሞት በኋላ ለአእምሮ ሕመም እንደተጋለጡ ይናገራል - መምህር ደበሎ።
ወደ መጨረሻም ሕመሙ ሲጠናባቸው ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ሰምቷል።
ከዚያም ዘመዶቻቸው በእጃቸው የነበረችውን የአንድ ዓመት ሕጻን በመቀበል ያሳድጉላቸው ጀመር።
“የጊምቢ አጠቃላይ ሆስፒታል ስሰራ በነበርኩበት ጊዜ አልፎ አልፎ ገንዘብ ሰጥቻቸው አልፍ ስለነበር እኚህ እናት ቀስ በቀስ አወቁኝ። ከዚያም ያናግሩኝ ጀመር። ብሎም ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ይፈልጉኝ ጀመር” በማለት እንዴት እንደተቀራረቡ ያስታውሳል።
እርሱም በበኩሉ ለእኚህ እናት ወደሚገኙበት ጎዳና ድረስ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ወስዶ ማስቀመጡን ገፋበት።
ከዚያ በኋላ ነው እኚህን እናት ከጎዳና ላይ አንስቶ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ቢደረግ የእምሮ ጤናቸው እንደሚሻሻል ያሰበው።
እናም ከወዳጆቹ ገንዘብ አሰባስቦ፣ በባለቤታቸው መሬት ላይ ባለ 28 ቆርቆሮ ቤት በመስራት ከጎዳና ተነስተው ወደ ቤታቸው እንዲገቡ አደረገ።
በመቀጠል ደግሞ ገና የአንድ ዓመት ልጅ እያለች ዘመዶቿ ወስደው ያሳደጓትን ልጃቸውን ከምዕራብ ወለጋ ላሎ አሳቤ ወረዳ በማምጣት ከእናትየው ጋር አገናኘ።
“በዚያን ሰዓት ልጃቸው ዘጠነኛ ክፍል ደርሳ ነበር። ልጅቱም መጥታ ከእናትየው ጋር ከተገናኙ በኋላ ሁለቱም ትልቅ ደስታ ተሰማቸው። ከዚያም በኋላ ልጅቱ እናቷን ትታ መመለስ አልፈለገችም” ይላል።
ይህ ቤተሰብም በቋሚነት ሕይወታቸውን መምራት እንዲያስችላቸው በማሰብ ከተለያዩ ወገኖች እርዳታ በማሰባሰብ ስድስት ክፍሎች ያሉት ቤት እንደሰሩላቸው እና ግማሹን በማከራየት ኑሯቸውን እየደጎሙ እንዳለ ይናገራል።
ልጃቸውም በጊምቢ ከተማ ትምህርቷን በመቀጠል በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት።

የፎቶው ባለመብት, Debelo Itana
መምህር ደበሎ አቅም ላጡ አቅም መሆንን የተማረው ገና አፍላ ጎረምሳ እያለ መሆኑን ያስታውሳል።
“ገና ዘጠነኛ ክፍል እያለሁ ነበር ሰዎችን መርዳት የጀመርኩት።”
እስካሁን ድረስም በምዕራብ እና በምሥራቅ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ 11 ቤተሰቦች ያዘመመ ቤታቸውን አቅንቷል፣ የፈረሰ ቤታቸውን አድሷል።
“ከእነዚያም መካከል ሦስቱ ከተሰራላቸው ቤት ገሚሱን በማከራየት በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን እየደጎሙ ይገኛሉ” ሲል ያክላል።
ቢቢሲ ገና በአፍላ ጎረምሳነት ሌሎችን ለመደገፍ ሰበብ የሆነህ ምክንያት አለህ ሲል ጠይቋል።
መምህር ደበሎ ይህንን ለማስረዳት ወደ ልጅነቱ ይመለሳል።
በ1981 ዓ.ም. ገና በእናቱ እቅፍ ሳለ ቤተሰቡ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ደጋፊነት ተጠረጠረ።
ከዚያም የወታደራዊው መንግሥት ወታደሮች “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ደጋፊዎች ናችሁ” በማለት የቤተሰቦቹን ቤት ማቃጠላቸውን ያስታውሳል።
“ከዚያ በኋላም እኛ ቤት አልባ ቤተሰብ፣ በመንገድ ላይ የተበተነ ቤተሰብ ሆንን። ከሦስት ሳምንት በላይም ዛፍ ስር ተጠልለን ኖረናል” ሲል በልጅነታቸው ያሳለፉትን ያስታውሳል።
“በልጅነቴ ያ ታሪክ በጣም ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም የነበረን ሀብት ሁሉ ጠፍቶ ባዷችንን በመቅረታችን የተነሳ፣ ከአንደኛ ክፍል እስከ ሦስተኛ ክፍል ቤተሰቦቻችን እንደሚፈለጉት እኛን ማስተማር አልቻሉም ነበር” በማለት ቤተሰቦቹ ያሳለፉትን ችግር ያስታውሳል።
በዚህም ምክንያት ቤት የሌላቸውን፣ አባት እና እናታቸውን በሞት ያጡ ልጆችን፣ በተለይም ‘እገሌ ቤቱ ተቃጥሎበታል፣ እገሌ ቤት የለውም መንገድ ላይ ይኖራል’ የሚባል ነገር ሲሰማ የቀደመ የልጅነት ቁስል ይሰማዋል።
በ1996 የዘጠነኛ ክልፍ ተማሪ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ የተቸገሩ ሰዎች ሲረዳ መቆየቱን የሚናገረው መምህር ደበሎ፣ “እኔ በውስጡ አልፌ ያደግኩበትን ሁኔታ የአሁኑ ትውልድ እንዲጋፈጠው ስለምፈልግ ቤት ለሌላቸው ሰዎች ቤት የመሥራት ፕሮግራም አውጥቼ ጀመርኩኝ” ይላል።
ይህ ግን ሁል ጊዜም አልጋ በአልጋ አይደለም።
በእጁ ላይ ያለውን ገንዘብ ለተቸገሩ ሰጥቶ ባዶ ኪሱን የቀረበት፣ በዚህም የተነሳ ደመወዝ እስኪደርስ ድረስ የተቸገረበት ጊዜ አለ።
ግን ደስታውን የሚሰፍረው በኪሱ ባለው ገንዘብ ልክ ሳይሆን ከገቡበት የችግር አረንቋ ባወጣቸው ሰዎች ልክ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Debelo Itana
የመምህር ደበሎ ልጅነት ቤት አጥቶ ዛፍ ተጠግቶ ማደግ ብቻ አይደለም። ከትምህርት ገበታ ላይ የተሟላ ነገር ሳይዙ መቅረብም ያሳለፈው እውነታ ነው።
ስለዚህ ተማሪዎችን መደገፍ ሌላው ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ነው።
በቅርቡም ከሁለት መቶ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሳርያዎችን ማበርከቱን ያስታውሳል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ያለውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ አንድ ደብተር ለመግዛት ከ55 እስከ 65 ብር እንደሚጠይቅ የሚናገረው ደበሎ፣ “በዚህ ዋጋ ደግሞ የዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰብ ልጆች መማር ይከብዳቸዋል ይላል።”
ይህንን ችግር የተረዳው መምህር ደበሎ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተማሪዎችን ለመርዳት በፌስቡክ ገፁ ላይ ተከታዮቹ የአቅማቸውን እንዲረዱት በመጠየቅ ከ123 ሺህ ብር በላይ ማሰባሰቡን ይናገራል።
በዚህም ገንዘብ “በጊምቢ፣ ደምቢዶሎ እና ቂልጡ ካራ የሚገኙ ከ200 በላይ እናትና አባት የሌላቸው እና የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ተማሪዎች ደብተርና እስክቢርቶ እንዲሁም የአካል ጉዳት ላለባቸው ተማሪዎች ደግሞ ቦርሳ” ጨምሮ ገዝቶ መስጠቱን ይናገራል።
“አንድን ልጅ ደብተርና እስክቢርቶ ገዝቶ ወደ ትመምህርት ቤት ለመላክ ቢያንስ ከ1000 ብር በላይ ይጠይቃል። ይህ ገንዘብ ደግሞ የሌላቸው ቤተሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ሦስት ወይንም ደግሞ አራት የሚማር ልጅ ያላቸው ቤተሰቦች ደግሞ ጫናው የበረታ ነው” ይላል።
ስለዚህም እኔ ለማድረግ የሞከርኩት በቤተሰቦች ላይ ያለውን ጫና በተወሰነ መልኩ ማቃለል ነው ሲል ያክላል።












