የዩክሬን የህዋ ሮኬቶች ፋብሪካ መመታትና የአሜሪካ ተጨማሪ የሳዑዲን ነዳጅ ፍለጋ

ዩክሬናዊ እናትና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ባለፈው አርብ አመሻሽ ላይ ሩሲያ በማዕከላዊ ዩክሬን በምትገኘው ዲኒፕሮ ከተማ ላይ በፈጸመችው የረዥም ርቀት የሚሳኤል ጥቃት ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።

የአከባቢው ባለሥልጣናት እንዳሳወቁት ሚሳኤሎቹ የጠፈር ሮኬቶችን እና ሳተላይቶችን የሚያመርት ፋብሪካን እንዲሁም በአቅራቢያው የሚገኝ ጎዳናን መትተዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ይህ ፋብሪካ ለዩክሬን የሚሳኤል ግብአቶችን እና የተለያዩ ክፍሎችን ይሰራ ነበር ብሏል።

የዲኒፕሮ ከተማ ሩሲያ ኃይሏን ባሰባሰበችበት ምሥራቃዊ ክፍል ጦርነቱን ሸሽተው የመጡ ዩክሬናውያን መጠለያም መሆኑ ተነግሯል።

ክላቭዲያ የተባለች ነዋሪ አንድ ሮኬት ከመስኮቷ ፊት ለፊት እንደወደቀ ተናግራለች።

“እንደዚህ ያሉ ጥቃቶችን ለማምለጥ የት መጠለል እንዳለብን ማወቅ ፈታኝ ነው። በቤታችን በታችኛው ክፍል፣ በቤቶች ጀርባ ሁሉም ነገር በጥቃቱ ይወድቃል፣ ይፈራርሳል” ስትል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግራለች።

ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን ዶንባስ አካባቢ የምታደርገው የምድር ጥቃት ቀዝቀዝ እያለ በአየር ላይ የምታደርሰው ጥቃት እየጨመረ መጥቷል። እነዚህ ጥቃቶች አብዛኛውን ጊዜ እየደረሱ ያሉት በከተሞች ማዕከላት ላይ ነው ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ከኪዬቭ በስተምዕራብ በምትገኘው ቪኒትሲያ ከተማ ሩሲያ ባደረሰችው የሚሳኤል ጥቃት 24 ሰዎች ተገድለዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ሳዑዲ አረቢያን ለምን ፈለጓት?

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ሳዑዲ አረቢያን ገዥ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዚዳንትነቱን መንበር በተቆጣጠሩበት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የሳዑዲ አረቢያን ገዥ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማንን ለማነጋገር ፈቃደኛ አልነበሩም።

የአሜሪካ የደኅንነትና የስለላ ድርጅት ልዑል አልጋ ወራሹ በሳዑዲው ተቃዋሚ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ እጃቸው አለበት ብሎ ያምናል። የጋዜጠኛው ግድያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ድንጋጤን እንዲሁም ውግዘት ማስከተሉ ይታወሳል።

ነገር ግን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት ያስከተለው ከፍተኛ መዘዝ ማሳያ የፕሬዚዳንቱ በመካከከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መጓዛቸው ነው።

ሁለቱ መሪዎች በጀዳ በሚገኘው ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ወዳጅነት ባለው መልኩ በጡጫ ሲነካኩ የሚያሳይ ፎቶ ወጥቷል።

እንዲህ ፕሬዚዳንቱን ውሳኔያቸውን ያስቀለበሰው ጉዳይ ምንድን ነው? ዋነኛ ማጠንጠኛው የነዳጅ ዋጋ ነው።

የዘይት፣ የነዳጅ በአጠቃላይ የኃይል ዋጋ በተወሰነ መልኩ ከዩክሬን ባለው ጦርነት  ምክንያት እያሻቀበ መጥቷል።

አሜሪካ ያንን ዋጋ ዋጋ ለማውረድ ሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ምርቷን እንድትጨምር ፍላጎት አላት።