ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተጎዱ እና የታመሙ ፍልስጤማዊያን በራፋ ድንበር በኩል ወደ ግብፅ እያመሩ ነው
ከስምንት ወራት በኋላ የራፋህ ድንበር መከፈቱን ተከትሎ 37 የተጎዱ እና የታመሙ ፍልስጤማዊያን ለሕክምና ወደ ግብፅ አቅንተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በኤክስ ገፁ እንዳመለከተው 34 ሕፃናት እና 3 አዋቂዎች ከ39 ረዳቶቻቸው ጋር ለሕክምና ወደ ግብፅ ሄደዋል።
የእስራኤል ኃይሎች ባለፈው ዓመት ግንቦት ጋዛ መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በፍልስጤምና በግብፅ መካከል ያለው ድንበር ተዘግቶ ቆይቷል።
በእስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም እንዲሁም የታጋቾች ልውውጥ ስምምነት መሠረት ነው ድንበሩ የተከፈተው።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ ምስሎች እንደሚያሳዩት ፍልስጤማዊያን ሕፃናት በቃሬዛ እና በአምቡላንስ ነው ድንበሩን የተሻገሩት።
"ይህቺን ቀን በጉጉት ስንጠብቃት ነበር" ትላለች ልጇ ጥቂቶችን በሚያጠቃ አውቶኢሚዩን በሽታ የተያዘባት እናት ማይኻድር አብዱል ጋኒ።
ማይ እንደምትለው ልጇ ሞአታሴም ላለፉት ሶስት ወራት በጋዛው ናስር ሆስፒታል ሲረዳ ቢቆይም ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ነበር።
"ስሙ ሕክምና በሚሰጣቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ በመካተቱ ፈጣሪ ይመስገን። ሕክምና አግኝቶ ስቃዩ ይገታል የሚል ተስፋ አለኝ" ትላለች።
ልጇ ወደ ግብፅ እስኪዘዋወር ድረስ ስቃይ ውስጥ እንደቆየ ይናገራል።
"ስንቀሳቀስ በጣም ያመኛል። አፌን ስለሚያመኝ ምግብ መብላት አልችልም። መጠጣ አልችልም። ምንም ነገር ማድረግ አልችልም" ይላል።
ሞሐመድ አቡ ጃላል ከታካሚዎች ጋር ለሕክምና ወደ ግብፅ ከሚሄዱ ሰዎች መካከል ነው። የአጎቱ ልጅ ላራ አቡ ጃላል በቦምብ ጥቃት ምክንያት ወላጆቿ እና ወንድሞቿ ሲሞቱ እሷ እግሯ ላይ ጉዳት ደርሶበታል።
"አንድ እግሯ በጣም ስለተጎዳ እንዲቆረጥ ሆኗል። እንዳይቆረጥ ብዙ ጥረት አድርገን ነበር ግን አልተሳካም። ምክንያቱም አጥንቷ ጋንግሪን ይዞት ነበር" ይላል።
"አንደኛው እግሯ ቢጎዳም ሕክምና ይፈልጋል። የተቆረጠው እግሯም ክትልል ያስፈልገዋል።"
ድንበር እየተሻገረ ሳለ ለቢቢሲ ቃለ-ምልልስ የሰጡት በዌስት ባንክ እና በጋዛ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ሪክ ፒፔር ሁሉም ነገር "በሥርዓት" እየተከናወነ ነው ብለዋል።
"አምቡላንሶች አንድ በአንድ እየሄዱ ነው። መራመድ የማይችሉ ታካሚዎች ቀድሞው ሄደዋል። መራመድ የሚችሉ ታካሚዎችና አጋዦቻቸው ተከትለዋል። ማጣራት ከተደረገባቸው በኋላ ወደ ግብፅ ያመራሉ።"
እሳቸው እንደሚገምቱት 14 ሺህ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ቢያስፈልጋቸውም ከጋዛ መውጣት አልቻሉም።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከታካሚዎቹ ግማሽ የሚሆኑት "ከጦርነት ጋር በተገናኘ ጉዳት ያጋጠማቸው፤ የሰውነት አካላቸው የተቆረጠ፤ እሳት ያቃጠላቸው፤ የጀርባ ሕመም ያጋጠማቸው" ሲሆኑ ኦፕሬሽንና ሌሎች ሕክምናዎች የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
"5 ሺህ የሚሆኑት ሕፃናት እንደሆኑ ግምት አለ።"
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አለቃ የሆኑት ካጃ ካላስ አርብ ዕለት እንዳሉት ሕብረቱ ዝውውሩን የሚመለከት ቡድን ወደ ራፋህ ድንበር ልኳል።
ራፋህ ድንበር በደቡብ በኩል ከጋዛ የሚያስወጣ ሲሆን ከጋዛ ሰርጥ ከሚያስወጡ ሁለት ድንደበር አንዱ ነው። ወደ እስራኤል የሚያስወጣው በሰሜን ጋዛ የሚገኘው ኤሬዝ ድንበር ሰዎች እና ዕቃ የሚተላለፍበት ነው።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ 47 ሺህ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።