የካናዳ የሰደድ እሳት ጭስ የሚሊዮኖችን ጤና ስጋት ላይ ጣለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በካናዳ የተቀሰቀሰው የሰደድ እሳት ጭስ በሰሜን አሜሪካ ባሉ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ጤና ላይ ስጋት መድቀኑ ተገለጸ።
የሰደድ እሳቱ ጭስ ቶሮንቶን ጨምሮ በኦንታሪዎ እና ኪዩቤክ ግዛቶች የሚገኙ ከተሞችን ሸፍኗል። ጭሱ ከካናዳ አልፎ በአሜሪካ ከተሞችም ደርሷል።
ከካናዳ በቅርብ ርቀት በሚገኙት ኒው ዮርክ እና ኮነቲኬት የአየር ሁኔታው ለጤና ተስማሚ ያልሆነ የሚል ደረጃ ወጥቶባቸዋል።
ኢንቫሮመንት ካናዳ የተባለው ተቋም በኦታዋ ያለው የአየር ጥራት ለጤና “እጅግ አደገኛ” ነው ሲል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
በቶሮንቶ እና አካባቢው ደግሞ የአየር ጥራቱ ለጤና “ከፍተኛ አደጋ” ተብሎ ተፈርጇል።
የአሜሪካው የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ በበኩሉ በሰሜን ምስራቅ የአሜሪካ አካባቢዎች ያለው የአየር ሁኔታ በተለይ ደግሞ ከመተንፈሻ ስርዓት ጋር የጤና እክል ላለባቸው ሰዎች “ጤናማ” አይደለም ብሏል።
የአየር ጥራታቸው ጤናማ አይደለም ከተባሉት የአሜሪካ ከተሞች ቦስተን እና ዋሽንግተን ዲሲን ይጨምራል።
ትናንት ማክሰኞ ኒው ዮርክ ከተማ በካናዳው የሰደድ እሳት ምክንያት በጭስ ታፍና ታይታለች።
የሁለቱ አገራት የጤና ኃላፊዎች በጭስ የተበከለው አየር የአጭር የረዥም ጊዜ የጤና እክል እንደሚያስከትል በመግለጽ ሰዎች ከቤት ውጭ የአካል እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ እና በተቻላቸው መጠን እራሳቸውን ለጭሱ እንዳያጋልጡ አሳስበዋል።
የአየር ጥራት መቀነስ የካናዳ መንግሥት በተለይ በኪዩቤክ ግዛት ከሚገኙ ከተሞች የአስም እና ሌሎች ከመተንፈሻ ስርዓት ጋር የተያያዘ ሕመም ያለባቸውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዘዋወር ተገዷል።
ካናዳ ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ በርካታ የሰደድ እሳት እያጋጠማት ነው። መጭው የበጋ ወራትም ደረቅ እና ሞቃታማ ስለሚሆን የሰደድ እሳት ስጋቶች መኖራቸው ተመላክቷል።
እስካሁን ድረስ የሰደድ እሳቱ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ፣ አልበርታ፣ ኦንታሪዮ፣ ኖቫ ስኮሺያ በተባሉ ግዛቶች 3.3 ሚሊዮን ሄክታር የሚሸፍን ቦታን አንድዷል።












