የእስራኤል መከላከያ አወዛጋቢ የሆነውን የዌስት ባንክ የሰፈራ መርሃ ግብር አፀደቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል ዌስት ባንክን ከእየሩሳሌም ሙሉ ለሙሉ የሚነጥለውን እና ግዛቶችን ለሁለት የሚከፍለውን አወዛጋቢ የሰፈራ መርሃ ግብር የመጨረሻ ይሁንታ ሰጠች።

'ኢ 1' የሚል ስያሜ ያለው ግንባታ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ስለገጠመው ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተስተጓጉሎ ቆይቷል።

ተቺዎች እቅዱ የፍልስጤም አገርነት ላይ ያለውን ተስፋን ያጨልማል በሚል ሲቃወሙት ቆይተዋል።

ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ኮሚቴ በ'ኢ 1' 3,400 ቤቶችን ለመገንባት የተያዘውን እቅድ አፅድቋል።

የቀኝ ዘመም ፖለቲከኛ የሆኑት የእስራኤል ገንዘብ ሚኒስቴር ብዛሌል ስሞትሪች እቅዱን ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረጉ ሲሆን የፍልስጤም አገርነት "እየተፋቀ ነው" ብለዋል።

የፍልስጤም ባለሥልናት እርምጃውን በማውገዝ፤ ሕገ ወጥ እና ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የሁለት አገር የመፍትሔ ሀሳብን "የሚያጠፋ" እንደሆነ ተናግረዋል።

የእስራኤል ውሳኔ ቁጥራቸው እየጨመረ ያሉ ዓለም አቀፍ አገራት የፍልስጤምን የአገርነት እውቅና ለመስጠት በይፋ ባሳወቁበት ማግስት የመጣ ነው።

እስራኤል በዌስት ባንክ እና ምሥራቅ እየሩሳሌም ወረራ ከጀመረች ወዲህ በ160 ሰፈራዎች ለ700 ሺህ አይሁዳዊያን ቤት ገንብታለች።

ጋዛን ጨምሮ እነዚህ መሬቶች ለፍልስጤም አገርነት የሚፈለጉ ግዛቶች ናቸው።

በእነዚህ አካባቢዎች 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማዊያን ይኖራሉ።

በዓለም አቀፍ ሕግ ሰፈራዎቹ ሕገ ወጥ ሲሆኑ፤ ይህ አቋም በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት አማካሪዎች ባለፈው ዓመት ድጋፍ አግኝቷል።

ተከታታይ የእስራኤል መንግሥታት ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ መስፋፋቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ሰፈራ አራማጅ የሆነውን ቀኝ ዘመም ጥምረት መርተው ወደ ሥልጣን ከወጡ እ.አ.አ ከ2022 ወዲህ እና በሐማስ ጥቃት ከተቀጣጠለው የጋዛ ጦርነት በኋላ ጨምሯል።

በምሥራቅ እየሩሳሌም እና 'ማሌ አዱሚን' ሰፈራ መሀል 12 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው 'ኢ 1' የሰፈራ መርሃ ግብር 3,401 ቤቶችን የሚገነባ ሲሆን፤ ከሕዝባዊ አስተዳደር ከፍተኛ የእቅድ ካውንስል ፈቃድ አግኝቷል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ኮሚቴ በተጨማሪም በደቡባማ ዌስት ባንክ ካለ መንግሥት ፈቃድ ውጭ ተገንብቶ ባለፈው ግንቦት በእስራኤል ሕጋዊ በተደረገው አካባቢ 342 ቤቶችን ለመገንባት ፈቅዷል።

የሕዝባዊ አስተዳደር ቢሮን የሚመሩት ብዛሌል ስሞትሪች "የፍልስጤም አገርነት ከምድር እየተፋቀ ነው፤ በመፈክር ሳይሆን በእርምጃ" ሲሉ ተናግረዋል።

"እያንዳንዱ ሰፈራ፤ እያንዳንዱ መኖሪያ ሰፈር፤ እያንዳንዱ ቤት ለአደገኛ ሀሳብ ሌላ መቀበሪያ ነው" ብለዋል።

ሚኒስትሩ ኔታኒያሁ እርምጃውን እንዲያጠናቅቁ እና በይፋ ዌስት ባንክን የእስራኤል አባሪ ግዛት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

እስራኤል እ.አ.አ በ1980 ምሥራቅ እየሩሳሌምን በተሳካ ሁኔታ የግዛቷ አካል ያደረገች ሲሆን፤ ይህ እርምጃዋ በሰፊው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ያገኘ አይደለም።

የ'ኢ 1' መርሃ-ግብር ተቃዋሚዎች የዌስት ባንክን ሰሜናዊ ክፍል ከደቡቡ ይነጥላል በሚል የፍልስጤምን የአገርነት ምስረታ ሙሉ ለሙሉ የሚያግድ ነው እያሉ ነው።

በተጨማሪም ማዕከላዊ የሆነ የፍልስጤም ከተሞችን ልማት የሚያስተጓጉል ነውም ብለዋል።

የሰፈራ ተቃዋሚ የሆነው የእስራኤል ተሟጋች ድርጅት 'ፒስ ናው' በጦርነት ሽፋን ስሞትሪች እና ደጋፊዎቻቸው እያደረጉት ነው ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ አደገኛነቱን አስጠንቅቋል።

"የኢ 1 ዋነኛ ዓላማ የፖለቲካ መፍትሔን ማኮላሸት እና ሁለገብ አፓርታይድ መንግሥት ለመመስረት የሚደረግ መጣደፍ ነው" ብሏል።

በእስራኤል ቁጥጥር ስር ያልሆነውን የዌስት ባንክን ከፊል ግዛት የሚያስተዳድረው የፍልስጤም መንግሥት እግዱን አውግዟል።

"ይህ እቅድ እየሩሳሌምን ከፍልስጤም አካባቢዎች በግዝፍ የሰፈራ ግንባታዎች የሚነጥል ነው" ያለ ሲሆን፤ የተበታተነውን ዌስት ባንክ ክፍት እስር ቤት በማስመሰል ይከፍላል ሲል የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የእቅዱ መፅደቅ እስራኤል ለረጅም ጊዜ ስትከሰስበት የነበረውን እና የምትክደውን "በሰፈራ ወንጀል ይፋዊ የእስራኤል ተሳትፎን፣ አካባቢን መያዝ፣ የዘር ፍጅት እና በኃይል ማፈናቀልን" የሚያሳይ ነውም ብሏል።

ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የእስራኤልን "የቅኝ ግዛት እቅዶች" የሚያስቆም እርምጃ ዓለም አቀፉ ማኅበተሰብ እንዲወስድም ጥሪ አቅርቧል።

የዩናይትድ ኪንግደም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ እቅዱ የሚተገበር ከሆነ ፍልስጤምን ለሁለት የሚከፍል ነው ካሉ በኋላ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ እና የሁለት አገር መፍትሔን የሚያዳክም ነው ብለዋል።

"የእስራኤል መንግሥት ይህን ውሳኔውን መቀልበስ አለበት" ሲሉም አክለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህን ጥሪ በማስተጋባት "ሕገ-ወጥ' ሰፈራን የማስፋፋት ውሳኔ ይቀልበስ ብለዋል።

ከአሜሪካ እስካሁን አስተያት አልተሰጠም።

ይሁን እንጂ ሰኞ ዕለት በእስራኤል ጦር ሬዲዮ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በ'ኢ 1' ሰፈራ ላይ ስላለው አቋም የተጠየቁት አምባሳደር ማይክ ሀክቤ፤ ግዙፍ ልማት በ'ኢ 1' ይኑር አይኑር የእስራኤል መንግሥት የሚወስነው ውሳኔ ነው ብለዋል።

"እንደ አጠቃላይ ሕግ [ሰፈራው] ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ አይደለም። እስራኤላዊያን በእስራኤል እንዲኖሩ እውቅና መስጠት እና መፍቀድ አለብን" ሲሉም አክለዋል።

ባለፈው ዓመት ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በሰጠው ምክራዊ አስተያየት በተያዙ የፍልስጤም ግዛቶች የቀጠለው የእስራኤል እንቅስቃሴ ሕገ ወጥ ነው ብሏል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ፍርድ ቤቱ "የውሸት ውሳኔ" ወስኗል ያሉ ሲሆን፤ አይሁዳዊያን በገዛ መሬታቸው ወራሪ አይደሉም ብለዋል።