ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን የግድያ ሙከራ ልታደርግ ትችላለች በሚል የትራምፕ ደኅንነት ከሳምንታት በፊት ተጠናክሮ እንደነበር ተሰማ
ኢራን የግድያ ሙከራ ልታደርግ ትችላለች በሚል ስጋት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፀጥታ ቡድን ከሳምንታት በፊት እንዲጠናከር ተደርጎ እንደነበር የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የደኅንነት ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት ኢራን ልትፈጽመው ትችላለች የተባለው የግድያ ሙከራ እና ዶናልድ ትራምፕ ላይ ባለፈው ቅዳሜ የደረሰባቸው የግድያ ሙከራ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር እስካሁን አልተገኘም።
ቢሆንም የትራምፕ ጥበቃ ተጠናክሮ ሳለ የ20 ዓመቱ ቶማስ ማቲው ክሩክስ እንዴት ፕሬዝዳንቱ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ሥፍራ ተገኝቶ እንደተኮሰባቸው አሁንም አጠያያቂ ሆኗል።
የዩኤስ ሚስጥራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እና የዶናልድ ትራምፕ ጥበቃ ቡድን አባላት ከኢራን ሊሰነዘር ይችላል ስለተባለው ጥቃት መረጃ ደርሷቸው ነበር።
ይህን መረጃ ተከትሎ የዶናልድ ትራምፕ ጥበቃ እንዲጠናከር መደረጉን የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
የደኅንነት ምንጮች ሲቢኤስ ለተባለው የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሚድያ እንደተናገሩት ሚስጥራዊው የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባለፈው ሰኔ ነው ጥበቃውን ያጠናከረው።
ከኢራን ሊመጣ ይችላል የተባለው ጥቃት ለመመከት ተጨማሪ ደኅንነቶች፣ አልሞ ተኳሾች፣ ድሮኖች እና የሮቦት ውሾች እንዲጠናከሩ ተደርጎ ነበር።
ሲቢኤስ እንደዘገበው ኢራን ጥቃት ልታደርስ ትችላለች የሚለው ፍራቻ የመጣው “ከሰዎች በተገኘ መረጃ” መሠረት እንዲሁም ኢራናዊያን ትራምፕ ላይ ጥቃት ማድረስን በተመለከተ ካደረጉት ውይይት ነው።
የኢራኑ ኩድስ ኃይል አዛዥ የነበሩት ቃሲም ሱሌማኒ በትራምፕ ትዕዛዝ በአውሮፓውያኑ 2020 በድሮን ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።
ይህን ግድያ ያዘዙት በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ እና የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ከቴህራን ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የኢራን ሚሽን ዘገባውን “መሠረት የሌለውና ተጨባጭ ያልሆነ” ሲል ካጣጣለው በኋላ ትራምፕ “ወንጀለኛ ነው፤ በሕግ ፊት ነው መቀጣት ያለበት” ብሏል።
የአሜሪካ ሚስጥራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቃል-አቀባይ አንተኒ ጉግሊየልሚ እንደሚሉት የሳቸው መሥሪያ ቤት እና ሌሎች የደኅንነት ኤጀንሲዎች “በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎች የሚደርሷቸው” ሲሆን ጥቃት እንዳይደረስ ቅድመ-ጥንቃቄ ያደርጋሉ።
“ይደርሳሉ ስለተባሉ ጥቃቶች አሰተያየት አንሰጥም። ነገር ግን የደኅንነት መሥሪያ ቤታችን ዛቻዎችን በቀላሉ አይመለከትም፤ አስፈላጊውን ምላሽም ይሰጣል” ብለዋል።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ በቢቢሲ ቢጠየቅም ስለደኅንነት የሚመለከተው መሥሪያ ቤቱ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አድሪየን ዋትሰን እንዳሉት የአሜሪካ የደኅንነት ባለሥልጣናት “የቀድሞ የትራምፕ አስተዳደር አባላት ላይ ኢራን የምታደርሰውን ዛቻ ለዓመታት ሲከታተሉ ነበር።”
“ዛቻው የሚመነጨው ኢራን የሱሌማኒን ግድያ ለመበቀል ካላት ፅኑ ፍላጎት ነው” ያሉት ቃል-አቀባይዋ ክሩክስ የተባለው ግለሰብ “ባደረሰው ሙከራ እና በኢራን መካከል ግንኙነት መኖሩን የሚያሳይ መረጃ አለመኖሩን” ጠቁመዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር የኢራን ኢስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አባላት ላይ የወንጀል ክስ መሥርቶ እንደነበር አይዘነጋም።
ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካዋ ፔንሲልቬኒያ ግዛት የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የደረሰባቸውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ እንዴት ፖሊስ እና የደኅንነት አባላት ይህንን መመከት አቃታቸው የሚለው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
የሚስጥራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር እንዳመኑት ክሩክስ ከ130 ሜትር ርቀት ትራምፕ ላይ ሲተኩስ ፖሊሶች በሥፍራው ነበሩ።
ፕሬዝዳንት ባይደን ታጣቂው እንዴት አድርጎ ትራምፕ የግድያ ሙከራ ሊያደርስ እንደቻለ የሚመረምር ገለልተኛ ታዛቢ እንዲቋቋም ያዘዙ ሲሆን ሚስጥራዊ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ደግሞ ከኮንግረስ አባላት ጥያቄዎች ይጠብቁታል።