የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት፡ ‘ፑቲን አብዛኛውን ዩክሬንን ለመጠቅለል ዕቅድ አላቸው”

ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን አብዛኛውን የዩክሬንን ክፍል ጠቅልለው ለመያዝ ፍላጎት እንዳላቸው ደርሼበታለሁ ሲል የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

ይሁንና የሩሲያ ወታደሮች እስከ አሁን ባደረጉት ጦርነት እጅግ በመዳከማቸው ከዚህ ወዲህ የዩክሬንን ይዞታ ለመውሰድ በጣም አዝጋሚ እንደሚሆኑ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ጠቁሟል።

ይህ ማለት የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ከሚገመተውም በላይ እጅግ የተራዘመ ጊዜን ሊወስድ ይችላል።

በመጋቢት ወር ሞስኮ ትኩረቴን ከዚህ ወዲያ ከኪየቭ አንስቼ ወደ ዶንባስ ክፍለ ግዛት አዙሪያለሁ ማለቷ አይዘነጋም።

ይህም ዋና ከተማ ኪየቭን ለመያዝ ያደረገችው ሙከራ ውጤት ባለማስገኘቱ ነበር።

ይሁንና ፑቲን ጦርነቱ ሲጀመር የነበራቸው ፍላጎት አሁንም ድረስ እንዳለ ነው ሲሉ የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረባ ሚስ ሃይነስ ተናግረዋል።

ይህ የፑቲን ሕልም ደግሞ አብዛኛውን የዩክሬን ግዛት ጠቅልሎ በእጅ ማስገባት ነው።

ይሁንና ይላሉ ሚስ ሃይሰን፣ ይሁንና የፑቲን ሕልምን ለማሳካት ጦርነቱ ለሞስኮ እጅጉኑ ይከብዳታል።

“እንደምንረዳው ከሆነ በፑቲን ሕልምና መሬት ላይ ባለው የወታደራዊ አቅም መካከል ሰፊ ርቀት መኖሩን ነው’ ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ሞስኮ ትኩረት ያደረገችበት ክፍለ ግዛት ዶንባስ ሰፊ የኢንዱስትሪ አካባቢ ሲሆን ፑቲን በዶንባስ በሚገኙ የሩስኪ ተናጋሪዎች ላይ ዩክሬን  የዘር ማጥፋት ዘመቻን አካሄዳለች ብለው ይከሳሉ።

የሩሲያ ወታደሮች በዶንባስ ክፍለ ግዛት ከብዙ ትግል በኋላ የተወሰኑ ከተሞችን መቆጣጠራቸው የተዘገበው ከሳምንት በፊት ነበር።

ይህም ወታደራዊ ስኬት የሰቨዶኔስክ ከተማን ይጨምራል።

ቢሆንም ግን የሩሲያ ወታደሮች ከተማውን ለመቆጣጠር የወሰደባቸው ጊዜ ረዥም የሚባል ሲሆን የዩክሬን ወታደሮች ያልተጠበቀ ጠንካራ መከላከል ነበር የገጠማቸው ትላለች አሜሪካ።

አሁን የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደሚገምተው ከሆነ የሩሲያ ወረራ ግቡን ለመምታት ከዚህም በላይ የተራዘመ ጦርነት ሊያስፈልግ ይችላል።

መሬት ላይ የሚኖረው አቅም እስከ አሁን ካለው የከፋ እየሆነ እንደሚመጣም ይተነብያል።

‘ሩሲያ እንደምታስበው ትልቅ ድል አታገኝም፣ የተራዘመ ጦርነት ግን ይኖራል’ ብለዋል የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ ሚስ ሃይነስ።

የኔቶ አባል አገራት ከሰሞኑ ለዩክሬን የሚያደርጉትን እርዳታ መቼም ቢሆን እንደማያቋርጡ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

ኔቶ አባል አገራት ፊንላንድና ስዊድንን ወደ ቡድናቸው በይፋ የጋበዙ ሲሆን የወታደር እንቅስቃሴ በማድረግ በድንበር አገራት የሚኖረውን ጦር ለማስፋትና ለማጠናከርም አልመዋል።

ባይደን በበኩላቸው ኔቶ በምድር በአየርና በባሕር በሁሉም አቅጣጫ ወታደሮቹን ያጠናክራል ብለዋል።

የኔቶ ዋና ጸሐፊ ደግሞ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ኔቶ እንዲህ የተጠናከረበት አንድም ወቅት የለም ብለዋል።

የፊንላንድና ስዊድን ወደ ኔቶ መጠጋት ያስቆጣቸው ፑቲን ኔቶ ሆን ብሎ ውጥረት እንዲነግስ እያደረገ ነው ብለዋል።

“የኔቶ ወታደሮች ከተንቀሳቀሱ ሩሲያ ምላሸ ለመስጠት ትገደዳለች’ ብለዋል ፑቲን።

ይህ በእንዲህ እያለ የዩኬ መንግሥት 1 ቢሊዮን ፓውንድ ለዩክሬን ለግሷል።

 እስከ አሁን ከዚህ የሚስተካከል እርዳታ ለዩክሬን የሰጠችው አሜሪካ ብቻ ናት።

ከምዕራብ አገራት ወታደራዊ እርዳታ በገፍ እያገኘች ያለችው ዩክሬን ግን ይህ በቂ አይደለም ትላለች።

ፕሬዝዳንት ዘለነስኪ አገራቸው ለጦርነቱ በወር በትንሹ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት የተናገሩት ከሰሞኑ ነበር።