ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
9 ሰዎችን 'የበላው' ነብር በ200 ፖሊሶች ታድኖ ተገደለ
የሕንድ ፖሊስ 9 ሰዎችን የገደለውን ነብር ተኩሶ ገደለ።
በአካባቢው ማሕብረሰብ ‘የቻምፓራን ሰው በላ’ እየተባለ ሲጠራ የነበረው ይህ ነብር፤ ለሰዎች ስጋት ተደርጎ በ200 ፖሊሶች ሲታደን ነበር።
ነብሩ የተገደለው በቢሃር ግዛት ቻምፓራን በሚባል ቦታ ነው።
ከፖሊሶቹ ውስጥ የተወሰኑት በዝሆን ታጅበው ነበር ነብሩን ሲያድኑ የነበረው።
ይህ ወንድ ነብር በቫልሚኪ የታይገር ማቆያ የነበሩ የአካባቢው ሰዎችን ሲያሸብር ነው የኖረው ተብሏል።
ሕንድ በዓለም ላይ ከሚገኙ የዱር ነብሮች 70 ከመቶ የሚሆኑት የሚገኙባት አገር ናት።
ሕንድ እነዚህን ነብሮች የምታቆይባቸው ቦታዎች ከነብሮች ቁጥር መበራከት ጋር በሚመጣጠን መልኩ አለማስፋቷ ነብሮች ቁጡ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ነው ተብሏል።
በዚህ የተነሳ ነብሮቹ ሰዎች ወደሚኖሩበት ሰፈር አምጸው በመሄድ የቀንድ ከብትና ሰዎችን መግደል ጀምረዋል።
ይህ 9 ሰዎችን የገደለው ነብር 200 ፖሊሶች ሲከታተሉት ቆይተዋል።
ኦፕሬሽኑ የተመራው በቢሃር ግዛት ፖሊስ ሲሆን በመጨረሻ በአንድ የሸንኮራ አገዳ ሜዳ ሲታልቶላ ባሉዋ በሚባል ቀበሌ ተይዟል።
ይህ የሦስት ዓመት ዕድሜ የነበረው ነብር ቲ-104 በሚል ኮድ ይታወቃል።
ኪማር ጉብታ የተባሉ የግዛቱ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ኃላፊ ለታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ጋዜጣ እንደተናገሩት ይህ ነብር ለሰው ልጅ ጠንቅ ተደርጎ ሲፈለግ የነበረ ነው።
ይህን ነብር በይፋ የማደን ሥራ የተጀመረው አንድ እናትን ከነልጇ ካጠቃ በኋላ ነው፥።
ከዚያ በኋላ በዚያ አካባቢ እንቅልፍ አልነበረም ተብሏል።
ነብሩን አባብሎ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገው ጥረት ሊሰምር አልቻለም። ይህም የሆነው ነብሩ ምንም ዓይነት ፍርሃት ያልፈጠረበት መሆኑ ነው ብለዋል ሚስተር ጉብታ።
በመጨረሻም ቅዳሜ 9፡15 ላይ ነብሩ በተኩስ እሩምታ ተገድሏል።
በሕንድ በየዓመቱ ከ40 እስከ 50 ሰዎች በነብር ይገደላሉ።