ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬኖች ኼርሶንን በመቆጣጠራቸው ደስታቸውን እየገለጹ ነው
ሩሲያ ከኼርሶን መውጣቷን ተከትሎ በርካቶች ደስታቸውን ለመግለፅ በአደባባይ ላይ መውጣታቸውን ቢቀጥሉም “ጦርነቱ አላበቃም” ሲሉ የዩክሬን ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል።
በደስታ የተሞሉ ነዋሪዎች የዩክሬን ወታደሮችን ወደ ከተማዋ ሲገቡ ተቀብለዋቸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ እና ኦዴሳን ጨምሮ በርካቶች በተመሳሳይ ደስታቸውን መግለጻቸው ተዘግበዋል።
ሞስኮ የምኞቷ ባይደርስም የዩክሬን ባለሥልጣናት ጥንቃቄ ያስፈልጋል እያሉ ነው።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር አማካሪ ዩሪ ሳክ "ለመዝናናት በጣም ገና ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሁልጊዜ ኼርሶን ነፃ እንደምናወጣ እናምን ነበር። አሁን ሩሲያውያን ይህን ጦርነት በፍጹም ማሸነፍ እንደማይችሉ ማመን መጀመራቸው እርግጠኞች ነን። ድንጋጤውን በየደረጃው እያየን ነው። በፕሮፓጋንዳ ሰዎቻቸውም ውስጥ መሸበርን እናያለን” ሲሉ ለሬዲዮ 4 ቱዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።
“በእርግጥ ይህ በጣም አስፈላጊ ድል ነው። ነገር ግን ... ይህ ጦርነት ገና አልተጠናቀቀም" ብለዋል።
ኼርሶን የውሃ፣ የመድሃኒት እና የምግብ እጥረት ቢያጋጥማትም የአደጋ ጊዜ አቅርቦቶች ከሚኮላይቭ መምጣት መጀመራቸውን የከተማዋ ከንቲባ ረዳት ተናግረዋል።
ረዳቱ ሮማን ጎሎቭንያ እንዳሉት ከጦርነቱ በፊት ከነበረው 320 ሺህ ሕዝብ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ70-80 ሺህ የሚሆኑት ሰዎች በኼርሶን ይኖራሉ።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው "ወራሪዎች ከኼርሶን ከመሸሻቸው በፊት ሁሉንም ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን አውድመዋል” ብለዋል።
ከተማዋ መቼ መብራት እንደምታገኝ እስካሁን አልተገለጸም። የሃይል መቆራረጡ የኼርሶን ዳቦ መጋገሪያዎች እንዳይሠሩ እንቅፋት ሆኗል።
የዩክሬን ኃይሎች በኼርሶን እና አካባቢው የተቀበሩ የሩሲያ ፈንጂዎችን እና ወጥመዶችን የማፍረስ ትልቅ ሥራ መጀመራቸውን ዜለንስኪ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለብዙ ዩክሬናውያን ቁልፍ የዜና ምንጭ የሆነው የዩክሬን ቴሌቪዥን በአካባቢው ስርጭቱን ቀጥሏል።
ዩሪ ሳክ የሚሳኤል ጥቃት ቀጣይ ስጋት እንዳለ አስጠንቅቀዋል። ሩሲያ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ሚሳይሎችን በመተኮስ የሃገሪቱን ኃይል በእጅጉ ጎድታለች።
የኪዬቭ አካባቢ ወታደራዊ አመራር የሆኑት ኦሌክሲ ኩሌባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ባለፈው ወር በዩክሬን ሠላማዊ መንደሮች ከፍተኛ ድብደባ አይተናል። አሁን መናገር የምፈልገው በኪዬቭ ክልል ላይ የሚደርሰው የሮኬት ጥቃት ስጋት አሁንም ከፍተኛ መሆኑን ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት የቀድሞ ኃላፊ ኦሌክሳንደር ዳኒሊዩክ ከኼርሶን ያፈገፈጉት የሩሲያ ወታደሮች የዲኒፕሮ ወንዝን አቋርጠው በግራ በኩል ወደ ጥልቅ መከላከል እንደሚገቡ ለቢቢሲ አስጠንቅቀዋል።
ሞስኮ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች እና ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ ወታደራዊ የጦር መሳሪያዎች እና ሌሎች ንብረቶች መውጣታቸውን ገልጻለች ።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቀው የሩሲያ ወታደሮች የማፈግፈግ አካል በማድረግ በዲኒፕሮ ወንዝ ላይ የመንገድ እና የባቡር ድልድዮችን የማውደም ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። አርብ
የወጡ ምስሎች በዋናው ወንዝ መሻገሪያ አንቶኒቪስኪ ድልድይ በከፊል መውደሙን ቢያሳዩም ጉዳቱ እንዴት እንደተከሰተ ግን ግልፅ አይደለም ።
በቢቢሲ ያረጋገጠው አዲስ የቪዲዮ ምስል በግድቡ አንድ ጫፍ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ መከሰቱን ያሳያል።
ዩክሬን እና ሩሲያ ግድቡን በፈንጂዎች ለመምታት ታቅዷል በሚል እርስ በእርሳቸው ሲካሰሱ ቆይተዋል። ግድቡ ከተመታ በኼርሶን ክልል የጎርፍ አደጋ ያስከትላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።