ኤሎን መስክ የግል ጀቱን የሚከታተለውን የትዊተር ገጽ ባለቤት ሊከስ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤሎን መስክ በግል ጀቱ የት እንደተጓዘ የሚከታተለውን የትዊተር ገጽ ባለቤት ሊከስ ነው።
የግል ጀቱ እንቅስቃሴ @ElonJet account በሚባለው ገጽ ለሕዝብ ይፋ መደረጉ የልጁን ደኅንነት አደጋ ላይ እንደሚጥለው መስክ ተናግሯል።
ይህ የትዊተር ገጽ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት። በዚህ ሳምንት ገጹን ትዊተር አግዶታል።
የገጹ ባለቤት የ20 ዓመቱ ጃክ ስዊኒ ነው። በረራ የሚከታተሉ መተግበሪያዎችን ተጠቅሞ ነው የመስክን የግል ጀት የሚከታተለው።
የመስክለ ጀት ሲነሳና ሲያርፍ ትዊተር ገጹ ላይ ይጽፋል።
መስክ እንዳለው ስዊኒ እና ሌሎችም የፍርድ ቤት ክስ ይጠብቃቸዋል።
“ትላንት ማታ አንድ መኪና ልጄ ሊል ኤክስ ያለበትን መኪና ሲከታተል ነበር። እኔ መኪናው ውስጥ ያለው መስያቸው ነው” ብሏል መስክ።
የሰዎችን እንቅስቃሴ በቀጥታ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አደጋ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ገልጿል።
የመስክን ጀት የሚከታተለው ወጣት ፍሎሪዳ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነው።
ትዊተር ገጹን መርምሮ መርሕ ጥሶ በማግኘቱ እንዲዘጋ መወሰኑን ለሲኤንኤን ገልጿል።
ወጣቱ ቢል ጌትስ፣ ጄፍ ቤዞስ እና ማርክ ዙከርበርግን ጨምሮ የሌሎችም ሀብታም አሜሪካውያን የግል ጀት እየተከታተለ የሚጽፋበቸው የትዊተር ገጾች አሉት።
በተጨማሪም ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ሌሎችም ታዋቂ ግለሰቦች ጋር የሚገናኙ ገጾችም አሉ።
ሁሉንም ገጾች ትዊተር አስወግዷቸዋል።
መስክ እንዳለው፣ ወጣቱ ገጾቹን እንዲያጠፋ 5ሺህ ዶላር ለመክፈል ጠይቀውት ነበር።
ወጣቱ የክፍያ ጥያቄው ከቀረበለት በኋላ፣ ከፍያውን መፈጸም እንደማያስፈልግ በትዊተር በኩል እንደተገለጸ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
መስክ ከወር በፊት ገጹን ላለመሰረዝ ቢወስንም አሁን ግን “ሰዎች ያሉበትን ቦታ የሚያጋልጡ ገጾች የደኅንነት ስጋት ናቸው” ብሏል።
የትዊተር የደኅንነት ክፍል ባወጣው የተሻሻለ መመሪያ “የሌሎች ሰዎችን የግል መረጃ ያለ ፈቃዳቸው መለጠፍ ክልክል ነው” ብሏል።
መስክ ትዊተርን ከገዛው በኋላ የተለያዩ ለውጦችን እያደረገ ይገኛል።
ከግማሽ በላይ ሠራተኞቹን ከማባረሩ ባሻገር በሳን ፍራንሲስኮ ዋና ቅርንጫፍ ለሚገኙ ሠራተኞች የቤት ኪራይ መክፈል ማቆሙም ተዘግቧል።
ትዊተርን ከገዛ በኋላ ለኤሌክትሪክ መኪና አምራች ድርጅቱ ተስላ የሚሰጠው ትኩርት በመቀነሱ ኢንቨስተሮች ስጋት ገብቷቸዋል።
በዚህ ሳምንት በሦስት ተከታታይ ቀናት 22 ሚሊዮን ድርሻ የሸጠ ሲሆን፣ ይህም 3.58 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል። መስክ በተስላ ያለው ድርሻ 40 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።












