ኢየሩሳሌም ውስጥ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ በርካቶች ቆሰሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእየሩሳሌም ከተማ በተለያዩ አቅጣጫዎች ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው ቢያንስ ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት ገለጹ።
ጥቃት አድራሾቹ በታሪካዊው ዌስተርን ዎል አቅራቢያ በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በነበረ አውቶብስ ላይ ተኩስ ከፍተዋል ሲሉ የአደጋ ጊዜ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ፖሊስ ከጥቃቱ በኋላ የሸሹትን ታጣቂዎች ማፈላለግ ጀምሯል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ድርጊቱ የሽብር ጥቃት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩን ተናግረዋል።
የአምቡላንስ አገልግሎት ባለሙያው ማጌን ዴቪድ አዶም ሁለት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በማከም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተጎጂዎቹ ስድስት ወንዶች እና አንድ ሴት ሲሆኑ እየሩሳሌም ወደሚገኙ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውንም አክለዋል።
ምን ያህሉ ታጣቂዎች እንደነበሩ ግልጽ አይደለም። የዕብራይስጥ ሚዲያ እንደዘገበው ከሆነ ግን ፖሊስ ቢያንስ ሁለት ተጠርጣሪዎችን እየፈለገ ነው።
በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ በተለቀቀ ቪዲዮ በስፍራው በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ፖሊሶችን ተሰማርተዋል። የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም ምዕመናን ከዌስተርን ዎል ግቢ እንዳይወጡ ለአጭር ጊዜ መከልከላቸውን ዘግበዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ፖሊስ "አካባቢውን መጠበቅ፣ ጥቃቱን መመርመር እና የሸሹትን ተጠርጣሪዎች ማፈላለግ ጀምሯል" ብለዋል።
ታይምስ ኦፍ እስራኤል እንደዘገበው ቢያንስ አንደኛው ታጣቂ አውቶብሱ በቦታው እስኪደርስ ከመጠበቅ ባለፈ ተሳፋሪዎች በሚሳፈሩበት ወቅት ተኩስ ከፍቷል።
ዳንኤል ካኒየቭስኪ የተባለ አሽከርካሪ "አውቶብሱ ሞልቶ ተጨናንቆ ነበር በንጉስ ዳዊት መቃብር አውቶቡስ ፌርማታ ላይ እንደቆምኩ የተኩስ ድምፅ ሰማሁ፤ ሰዎች ይጮሃሉ። በአውቶቡሱ ውስጥ የነበሩ ሰዎችም ተጎዱ" ሲል ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ የጸጥታ ሃይሎች አሸባሪዎቹን ለመያዝ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በጥቃቱ የተሳተፈ ማንኛውም ሰው "በሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ጉዳት ዋጋ ይከፍላል” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ዌስተርን ዎል በአይሁድ እምነት ውስጥ ካሉት ቅዱስ ስፍራዎች አንዱ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በየዓመቱ ወደ ስፍራው ያቀናሉ።
ጥቃቱ የደረሰው በጋዛ 44 ሰዎች ከተገደሉ ከሳምንት በኋላ ነው።
ለሦስት ቀናት በዘለቀው ግጭት የእስራኤል ኃይሎች የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ (ፒአይጄ) መሪዎችን ዒላማ ሲያደርጉ ታጣቂዎችም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ተኩሰዋል።












