በቅጣት ከቼልሲ ጨዋታ ውጪ የሆነው ሮናልዶ ምላሽ ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዲስፕሊን ምክንያት ማንቸስተር ዩናይትድ ከቼልሲ ከሚያደርገው ጨዋታ ውጭ የታደገው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምላሽ ሰጠ።
ሮናልዶ ከትናንት በስቲያ ጨዋታ ሳይጠናቀቅ ስታዲየም ለቅቆ የወጣው “በወቅቱ በነበረው ሁኔታ” ምክንያት ነው ብሏል።
የማንችስተር ዩናይትዱ የፊት መስመር ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቡድኑ ረቡዕ ምሽት የነበረው ጨዋታ ሳይጠናቀቅ ስታዲየሙን ለቆ መሄዱ ይታወቃል።
ሮናልዶ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ስታዲየም ጥሎ እንዲወጣ እንዳደረገው ኢንስታግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ አመላክቷል።
በተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረው ፖርቹጋላዊ ቡድኑ ማንቸስተር ዩናይትድ ቶተነሃምን 2-0 እየመራ 89ኛው ደቂቃ ላይ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ሲወጣ ታይቷል።
ሮናልዶ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ በቀጥታ ወደ ልብስ መቀየሪያ ከሄደ በኋላ ከስታዲየሙ መውጣቱ ተገልጿል።
"በወከልኳቸው ቡድኖች ውስጥ ላሉ ወጣቶች ራሴን አርአያ ለማድረግ ሁልጊዜ እሞክራለሁ" ሲል ሃሙስ ምሽት በኢንስታግራም ገጹ አስፍሯል።
"ይህ ግን ሁል ጊዜም የሚቻል አይደለም። . . . አንዳንድ ጊዜ የወቅቱ ሁኔታ ያሸንፈናል” ሲል አክሏል።
“በካርሪንግተን (የዩናይትድ የልምምድ ቦታ) ጠንክሬ መሥራት እንዳለብኝ ይሰማኛል፣ የቡድን አጋሮቼን መደገፍ እና በማንኛውም ጨዋታ ዝግጁ መሆን እንዳለብኝ ይሰማኛል።"
"ለግፊቱ መልስ መሰጠት አማራጭ አይደለም፤ በጭራሽ አልነበረምም። ይህ ማንቸስተር ዩናይትድ ነው። እናም ሁሌም አንድ ሆነን መቆም አለብን። በቅርቡ እንደገና አብረን እንሆናለን።" ብሏል የዩናይትድ የፊት መምመር ተጫዋቹ።
ማንችስተር ዩናይትድ የ37 ዓመቱ ተጫዋች አሁንም የቡድኑ ወሳኝ አባል እንደሆነ ገልጿል። ተጫዋቹ ከቼልሲው ጨዋታ ውጭ የሆነው በዲሲፕሊን ጉዳይ መሆኑን ጠቁሟል።
በስታምፎርድ ብሪጅ የማይሳተፍበት ጨዋታ ትልቅ ሲሆን ዩናይትድ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቼልሲ በአንድ ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ይገኛል።
በስፐርስ ጨዋታ በመጠናቀቂያ ደቂቃዎች ተቀይሮ እንዲገባ ቢጠየቅም ፈቃደኛ አለመሆኑን በርካታ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
ዩናይትዶች ከተፈቀደላቸው 5 ቅያሬዎች ውስጥ ሦስቱን ብቻ ቢያደርጉም በ89ኛው ደቂቃ ሮናልዶ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ወደ መልሻ ክፍል አቅንቷል። ቀጥሎም በፍጥነት ከስታዲየም መውጣቱ ታውቋል።
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ሐሙስ ዕለት ጉዳዩን "እንደሚፈቱት” ተናግረው ነበር።
ሮናልዶ ማንቸስተር እሑድ ዕለት በሜዳው ከኒውካስትል ጋር 0 - 0 ሲለያይ ተቀይሮ በመውጣቱ የተሰማውን ቅሬታ አሳይቷል።
የቀድሞው የእንግሊዝ አጥቂ ጋሪ ሊንክከር የሮናልዶ ባህሪ ዩናይትድ በስፐርስ ላይ ያሳየውን አስደናቂ ብቃት ትኩረት እንዳሳጣ ተናግሯል።
"ይህ ተቀባይነት የሌለው ነው። በጣም ደካማ ነው" ሲልም ሊንከር በቢቢሲ ማች ኦፍ ዘ ዴይ ፕሮግራም ላይ ተናግሯል።
የቀድሞው የዌልስ አምበል አሽሊ ዊሊያምስ “ለማንቸስተር ዩናይትድ ታላቅ ምሽት ነበር። ተሰልፎ ባይጫወትም አሁንም ስለ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እንናገራለን” ብሏል።
የቀድሞ የእንግሊዝ ተከላካይ ሚካህ ሪቻርድስ “ቡድንህ ሲያሸንፍ ከስፖርቱ ታላላቆች አንዱ ይህን ማድረጉ ተስፋ አስቆራጭ ነው” ብሏል።
ሪቻርድስ አክሎም የሮናልዶ ባህሪ "አክብሮት የጎደለው ነው" እና በጥር የዝውውር መስኮትም እንዲለቅ ሊፈቀድለት ይገባል ብሏል።
ሪቻርድስ ለቢቢሲ ሬድዮ 4 እንደተናገረው “አሰልጣኙ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ከእሱ ጋር ችግር ውስጥ ገባ። በቅድመ-ውድድር ዘመንም ቀጠለ። አሁንም ያው ነው። እኔ እንደማስበው ይህ መፈታት ያለበት በአንድ መንገድ ብቻ ነው” ብሏል።
"በጥር የዝውውር መስኮት ሊለቁት ይገባል። የአሰልጣኙን ሥራ እያበላሸ በመሆኑ መለያየቱ ጥሩ ይመስለኛል።" ብሏል።
የቀድሞው የዩናይትድ ግብ ጠባቂ ፒተር ሽሚሼል ሮናልዶ እንደዚህ አይነት ባህሪው “ርዕሰ ዜና" እንደሚሆን ያውቅ ነበር ብሏል።
"በእሱ ቅር እንደተሰኘሁ መናገር የምችልበት የመጀመሪያ አጋጣሚ ነው። ስደግፈው ቆይቻለሁ። ያለበትንም ሁኔታ ተረድቻለሁ" ሲል ሽማይክል ለቢቢሲ ሬዲዮ 5 ቀጥታ ስርጭት ወቅት ተናግሯል።
"እኛ በሽግግር ላይ ነን። ማንቸስተር ዩናይትድ ከአሌክስ ፈርጉሰን መልቀቅ በኋላ አምስት አሰልጣኞች ቀያይሯል።”
"እኛ እንደዚህ አይነት ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች አያስፈልጉንም። ይህ ተስፋ አስቆራጭ ነው” ብሏል።












