ለ12ኛ ክፍል ፈተና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ሳምንት አለፋቸው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የነበሩ 395 ተማሪዎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለስ ሳይችሉ ባሉበት ከሳምንት በላይ ሆናቸው።

ከሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ተነስተው ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ለፈተና የገቡት ተማሪዎች ወደ መኖሪያቸው መመለስ ያልቻሉት በፀጥታ ስጋት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

ተማሪዎቹ ፈተናቸውን ከአንድ ሳምንት በፊት ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም. ያጠናቀቁ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገኛሉ።

ተማሪዎቹ የመጡበት የደራ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑ አልጋነሽ ተስፋዬ በፀጥታ ችግር ምክንያት ተማሪዎቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ አለመቻላቸውን አረጋግጠዋል።

የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በስፋት በሚንቀሳቀሱባት ደራ ወረዳ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከተቋረጠ ሰነባብቷል።

ተማሪዎቹ አገር አቀፉን የ12ኛ ክፍል ፈተና ለመውሰድ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ወደ ዩኒቨርስቲው የተወሰዱት በመከላከያ ሠራዊት አጀብ እየተጠበቁ ነበረ።

“በአካባቢያችን ያለው የሰላም ሁኔታ አስቸጋሪ ስለሆነ ተማሪዎች ወደ ሰላሌ የተወሰዱት በመከላከያ ታጅበው ነበር” ሲሉ አልጋነሽ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ከደራ ወረዳ ዋና ከተማ ጉንዶመስቀል የሆኑ 255 ወንዶች እና 140 ሴት ተማሪዎች አሁንም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸዋል።

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የኮሚኒኬሽን እና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር የሺመቤት ቦጋለም እንዲሁ፤ ከደራ ወረዳ የመጡ ተማሪዎች በስተቀር ለፈተና ወደ ዩኒቨርሲታቸው የገቡ ተማሪዎች በሙሉ ወደ መጡባቸው ቦታዎች መመለሳቸውን ተናግረዋል።

አሁን ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ ያልቻሉት ተማሪች “ሲመጡም በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው ነበር። አሁን ለመመለስ የደኅንነት ሁኔታው አመቺ ስላልሆነ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ይገኛሉ” ብለዋል።

ዶ/ር የሺመቤት ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ የመኝታ እና ምግብ አገልግሎት እያቀረበ ስለሆነ ተማሪዎቹ በዚህ ረገድ ምንም አይነት ችግር እየገጠማቸው አይደለም ብለዋል።

“ለተማሪዎቹ የሚያስፈልገውን ነገር ዩኒቨርሲቲው አመቻችቷል። ምግብ፣ የመኝታ ቦታ፣ ሕክምና እና ጥበቃ አላቸው” ብለዋል።

የደራ ወረዳ ትምህር ቢሮ እንዲሁ ተማሪዎቹን ለወላጆቻቸው ለመመለስ ከሚመለከተው አካል ጋር አብሮ እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው ትምህር ቢሮ ባልደረባ ተማሪዎቹ ወደ ወላጆቻቸው መመለስ እስኪችሉ ድረስ በዩኒቨርሲቲ እንደሚቆዩ ገልጸው፤ ለደኅንነታቸው ሲባል ግን ከዩኒቨርሲቲ ጊቢ እንዲወጡ እንደማይፈቅድላቸው ጨምር ተናግረዋል።

የደራ ወረዳ ዋና ከተማ ጉንዶመስቀል ከፊቼ ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ርቃ ትገኛለች። በወረዳዋ የፋኖ ታጣቂዎች በስፋት ይንቀሳቀሳሉ።

በተመሳሳይ ዞን ውስጥ ባሉት ወረ ጃርሶ፣ ዳገም እና ሂዳቡ አቦቴ በተባሉ ወረዳዎች ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ አልፎ አልፎም ወደ ደራ ወረዳ በመሻገር ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች እና ተጓዦች ላይ ተደጋጋሚ እገታዎች የሚፈጸሙ ሲሆን፣ ለማስለቀቂያም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቁ ይታወቃል።

ተማሪዎቹን በታጣቂዎች ከሚፈጸሙ ጥቃቶች እና እገታዎች ለመጠበቅ የመከላከያ ሠራዊት አጅቦ ወደ ፈታና ቦታ ያደረሰቸው ሲሆን፣ ፈተናውን ከጨረሱ በኋላ ግን ተመሳሳይ ጥበቃ ባለማግኘታቸው እና በፀጥታ ስጋት ምክንያት ወደ አካባቢው ያለው የትራንስፖርት አገልገሎት በመስተጓጎሉ ባሉበት ለመቆየት ተገደዋል።