በቻይና ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በመቶ ሺዎች አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ ነው

ታትሟል

በደቡባዊና ምሥራቃዊ የቻይና ግዛቶች ከባድ ዝናብ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት በማስከተሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢዎቹን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል።

በ50 ዓመት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወንዞች ከልካቸው በላይ ሞልተው ጎርፍ ያስከተሉ ሲሆን ተጨማሪ ሁለት ግዛቶችም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

በመንግሥት በሚተዳደረው ሚዲያ በተላለፉ ቪዲዮዎች፣ ተሽከርካሪዎች በውሃ ተውጠው እና የአደጋ ተካላካይ ሠራተኞች ሰዎችን ሲያሸሹ ታይቷል።

አካባቢው ከፈረንጆቹ 1961 ወዲህ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ዝናብ አስተናገዶ እንደማያወቅ ተጠቁሟል።

በወንዝ ዳርቻዎች እና በዝቅተኛ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ከፍታማ ስፍራ እንዲዘዋወሩ ተጠይቀዋል።

ጓንጉዶንግ በተሰኘቸው ግዛት የምትገኘው ሻውጓን ከተማ በአደጋው ክፉኛ ከተጠቁ ከተሞች አንዷ ስትሆን፣ አስተዳዳሪዎቿ ከተማዋ ከወራት በኋላ ከፍተኛ ዝናብ ማስተናገዷን ተከትሎ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያዎችን እያወጡ ነው።

በተቃራኒው ኪንጉያን በተሰኘችው ከተማ ለነዋሪዎች መጠነኛ ማስጠንቀቂያ እየደረሳቸው ይገኛል።

ቀድሞም ቢሆን በኮቪድ-19 ክልከላ የምርት እና ማጓጓዣ አገልግሎቱ እየተፈተነ የነበረበትን ጉዋንግዶንግ እና ጓዋንዥ ግዛቶች በሚያካልለው በታችኛው የፐርል ተፋስስ አደጋው የአቅርቦት መስተጓጎል ፈጥሯል።

በሌላ በኩል በሰሜናዊ ምሥራቅ በምትገኛው ጂያንግዢ ግዛት በዘጠኝ አውራጃዎች የሚኖሩ 485 ሺህ ሰዎች በጎርፍ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጎጂ መሆናቸውን ተከትሎ ባለሥልጣናት ከፍ ያለ ማስጠንቀቂያ እየሰጡ መሆኑን ዥንዋ ዘግቧል።

የዜና ወኪሉ 470 ሚለዮን የን ወይም 70 ሚለዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ጉዳት ማስከተሉን እና 43 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን እህል ማውደሙን ገልጿል።

በታችኛው እርከን የሚገኙ ባለሥልጣናት በቀጣይ ቀናት ሁኔታው ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ያሰወቁ ሲሆን የፐርል ወንዝ ተፋሰስ ውሃ ሊጨምር እንደሚችል እያሳሰቡ ነው።