ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው" አራት የዘመነ ሕዳሴ ሥዕሎች ከጣልያን ሙዝየም ተሰረቁ
በአውሮፓ በጥበብ እና ባህል አብዮት በሚታወቀው ሬነሳንስ ዘመን የተሠሩ አራት "ትልቅ ዋጋ ያላቸው" ሥዕሎች ሲሲሊ ከሚገኝ ሙዝየም መሰረቃቸውን የአገሪቱ የባህል ሚኒስትር አስታወቁ።
አሌሳንድሮ ጉይሊ እንደተናገሩት ማርያምን ከክርስቶስ ጋር የሚያሳይ ሥዕልን ጨምሮ አራት የሥነ ጥበብ ሥራዎች ተሰርቀዋል።
በጣልያናዊው አንቶኔሎ ደ ሜሲና የተሰሩት ሥዕሎች ከሙዝየም የተዘረፉት፣ ያለፈው ቅዳሜ ምሽት ነው።
ሌቦቹ የደኅንነት መቆጣጠሪያ ደውል ሳይሰማ በምን መንገድ ወደ ሙዝየሙ መግባት እንደቻሉ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ይገኛል።
በአውሮፓ ሙዝየሞች የሚፈጸሙ ዝርፊያዎች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ነው። ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የሥነ ጥበብ ውጤቶችም ተሰርቀዋል።
የጣልያኑ የዜና ወኪል አናሳ እንደዘገበው መርማሪዎች የመጀመሪያ ግምት ብለው ያስቀመጡት ሥዕሎቹ በጥቁር ገበያ የሥነ ጥበብ ሌቦች ተሰርቀው ሊሆን እንደሚችል ነው።
ማርያምን ከክርስቶስ ጋር የሚያሳየው ሥዕል ደኅንነቱ በተጠበቀ ሥፍራ ተቀምጦ ነበር። የተቀሩት ሥዕሎችም በእንጨት ሳጥን ውስጥ ስለተቀመጡ በቀላሉ ለማውጣት ያስቸግራል።
የሙዝየሙ ኃላፊ ማሪሳ ሜርኩሮ እንደተናገሩት ዝርፊያው የተፈጸመው ምሽት ላይ ነው።
"በተፈጠረው ነገር ደንግጠናል። ሙዝየሙ፣ ከተማው፣ ማኅበረሰቡ እና የሥነ ጥበቡ ዓለም ትልቅ ነገር አጥተዋል" ብለዋል።
ሠዓሊው በ15ኛው ክፍለ ዘመን በሲሲሊ ይኖር ነበር። በሬነሳንስ ሥነ ጥበብ ታዋቂ ሆኑት አንዱም ነው።
በአውሮፓውያኑ 1473 የተሠራው የማርያም እና ክርስቶስ ምሥል በበርካታ መላዕክት የታጀበ ነው። ሳንታ ማሪያ ለተባለ ገዳም ነበር ሥዕሉ የተሠራው።
በአንድ በኩል ክርስቶስ ልጅ ሳለ እና በሌላ በኩል ክርስቶስ በአዋቂ ዕድሜ ላይ ሆኖ የሚያሳዩት ሥዕሎችም በተመሳሳይ ወቅት ነው የተሠሩት።
ሥዕሎቹ መጠናቸው አነስተኛ መሆኑ ለግላዊ ፀሎት መሠራታቸውን ይጠቁማል።
የሜሲና ከንቲባ ፌድሪኮ ባሲል "በዚህ የከፋ ወንጀል በጣም ተናድጃለሁ" ብለዋል።
"የሜሲና ሕዝብ ንብረት ተመዝብሯል፤ ሜሲና ታሪኳ እንዲዘረፍ አትፈቅድም" ሲሉም ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት የጣልያን የሥነ ጥበብ ወንጀል ክፍል በፓርማ አቅራቢያ ከሚገኝ ሙዝየም የተሰረቁ ሦስት ሥዕሎችን ማግኘቱን አስታውቋል። እነዚህ ሥዕሎች በአውሮፓውያኑ 2026 መባቻ ነበር የተሰረቁት።
ሥዕሎቹ ወደ 9 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጡ ናቸው። የሙዝየሙ የደኅንነት መቆጣጠሪያ ደውል ባይጮህ ኖሮ ሌቦቹ ተጨማሪ ሥዕሎች ይዘርፉ እንደነበርም ተገልጿል።
አምና ከፈንሳይ ሉቭ ሙዝየም 88 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጡ ታሪካዊ ጌጣ ጌጦች መዘረፋቸውን ተከትሎ የሥነ ጥበብ እና ቅርስ የደኅንነት ጥበቃ መሣሪያዎች ጥንካሬ ላይ ጥያቄ ተነስቷል።